
የጤና ተቋማትን ለህክምና ዝግጁ ከማድረግ ባሻገር ለድንገተኛ የጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡና ወረርሽኝን መመከት የሚችሉ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በማህበረሰቡ ላይ የሚከሰቱ ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን አስቀድሞ በመተንበይ በመተንተንና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ማህበረሰቡን ከተለያዩ የጤና አደጋዎች መከላከል እንደሚገባ ጠቁመው በክልሉ ውስጥ 6 ሆስፒታሎች ላይ የተጀመሩ ጅምር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የጤና ተቋማት ለህክምና ዝግጁ ከመሆን ባለፈ ለድንገተኛ የጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ማህበረሰቡን ካልታሰበ የጤና ችግርና ወረርሽኝ መታደግ ይገባቸዋል ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከክልሉ የተለያዩ ሆስፒታሎች የመጡ የሆስፒታል ስራ አስኪያጆች፣ሜድካል ዳይሬክተሮች እንዲሁም የህብረተሰብ ጤና አደጋ ክትትል አስተባባሪዎች በተገኙበት PHEM at Health Facility በሚል ርዕስ የጤና ተቋማት ላይ ያተኮረ የማጠናከሪያ ስልጠና በዛሬው ዕለት እየተሰጠ ሲሆን ከስልጠናው በኋላ የጤና ተቋማት የበሽታዎችን ክስተት በመለየት፣የሞት ሁኔታ መረጃዎችን በመተንተን በቀጣይ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል የመረጃ ልውውና የምላሽ አሰጣጥ ሂደቱን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል።
ምንጭ – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት



