Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

ታካሚ ላይ በማተኮር እና የማህበረሰብ ተሳትፎን በማሳደግ፣ የቲቢን በሽታን ለመከላከል መስራት እንደሚገባ ተገለጸ ፡፡

CERPHI

የኢትዮጵያ የቲቢ ምርምር አማካሪ ምክር ቤት የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ እና 20ኛውን ዓመታዊ የቲቢ ምርምር ኮንፈረንስ ” ቲቢን ማጥፋት እንችላለን!” በሚል መሪ ቃል በድምቀት እየተካሄደ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ለቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ጠንካራ የአመራር ቁርጠኝነት እና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል ። የኢትዮጵያ የቲቢ መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ቀዳሚ ትኩረቱን በመሠረታዊ የጤና አጠባበቅ፣ በማህበረሰብ ተሳትፎ እና በፈጠራ ስራዎች ላይ ማድረጉንም አክለዋል። በተለይ በታካሚ ላይ ያተኮረ እንክብካቤ በመስጠት፣ የማህበረሰብ ተሳትፎን በማሳደግ፣ እና ፈጠራና ኢኖቬሽንን በመጠቀም ቲቢን ለማስቆም እየተሰራ ያለውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ የጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው እንደተናገሩት ኢንስቲትየቱ የቲቢ በሽታ ላይ ያተኮሩ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን መስራቱን አውስተው የጥናቶቹ ግኝቶች በሀገራቀፍ ደረጃ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ነበራቸው ብለዋል፡፡ በተለይም ዘመናዊ የጂኖሚክ ምርመራን (Genomic Surveillance) ጨምሮ የላቦራቶሪ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ በኩል ትልቅ ስኬት መመዝገቡን ገልጸዋል። በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በትብብር በመስራት በቲቢ በሽታ ዙሪያ ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮችን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡ ።

የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የጉባኤዉ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፣ ምክር ቤቱ ከተመሰረተበት እ.ኤ.አ 2001 ጀምሮ ምርምርን ከብሔራዊ የቲቢ መቆጣጠሪያ ጥረት ጋር በማያያዝ ረገድ የላቀ ሚና ሲጫወት መቆየቱን ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቲቪ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ እንዲሁም በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ በርካታ እርምጃች የወሰደች ሲሆን በዚህም አመርቂ ለውጦች መመዝገባቸውን አውስተዋል፡፡ ምክር ቤቱ ባለፉት 25 ዓመታት በምርምር እና በፖሊሲ መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ ረገድ ጉልህ ሚና ማበርከቱን ገልጸው ለቀጣይ የቲቢ ቁጥጥር ስራዎች የምርምር አመራር አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህ ጉባኤ በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎችን እና አጋር አካላትን በአንድ የሚያገናኝ እንዲሁም የእውቀት ሽግግር የሚያመቻች በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በዚሁ መድረክ ላይ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ፕሮፌሰር ነጻነት ወርቅነህ እንደገለጹት፣ በኦሮሚያ ክልል የበሽታውን ታማሚዎች የመለየት ምጣኔ ከ95 በመቶ በላይ የደረሰ እና የመፈወስ መጠኑ ደግሞ ከ98 በመቶ በላይ መሆኑን ገልጸው ይህም ከዓለም አቀፍ አማካይ ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር የላቀ ስኬት መሆኑ ተናግረዋል ።

በኢትየጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ሲካሶሎ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የቲቢን በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስኬቶች አበረታች ናቸው ያሉ ሲሆን የአለም ጤና ድርጅት የሚያደርጋቸውን ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው በርካታ በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎች የጥናት ውጤታቸውን ያቀረቡ ሲሆን በዘርፉ የሚሰሩ አጋር አካላትም ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *