
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጤናና ጤና ነክ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክቶሬት ሳምንታዊ የቅኝት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል ፡፡
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እንደተናገሩት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረዉን የወባ በሽታ ለመግታት ጫናዉ የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎችን በመለየት መከላከልን መሠረት ያደረገ የክትትል እና የቁጥጥር ስራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለህብረተሰቡ የወባ በሽታ የመከላከያ መንገዶችን በማስተማር እና ህመሙ ሲከሰት ፈጥኖ ወደ ህክምና ተቋሞ በመሄድ ህክምና እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ላይ የግንዛቤ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ አስረድተዋል ።
በየተቋሙ ጥራቱን የጠበቀ የላብራቶሪ ስራዎችን ተደራሽነት በማጠናከር የወባ ጫናን በዘላቂነት ለማጥፋት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
የስርዓተ ምግብ ጫና ያለባቸው አከባቢዎችን የልየታ ስራ ላይ ማተኮር ተገቢ ነዉ ያሉት አቶ ማሙሽ በምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በልዩ ትኩረት መሰራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
አቶ ማሙሽ ለኬሚካል መመረዝ የተጋለጡ ሰዎችን በመለየት አስተማሪ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በመፍጠር ከችግሩ ፈጥነዉ እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል
አቶ ማሙሽ አክለዉም የኤች አይቪ ኤድስ በሽታ የሚያስከትለውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲሁም ስነልቦናዊ ጫናን ለመቀነስ በቫይረሱ አዲስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በጊዜ መከታተልና መቆጣጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ወቅቱን የጠበቀ መረጃን በጥራት በማደራጀት በመተንተን እና በተገቢው በመያዝ ጥቅም ላይ የማዋል ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ አቶ ማሙሽ ጠቁመዋል ።
በመድረኩ በክልሉ የወባ ወረርሽኝና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በሳምንቱ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በሸምሲያ አደም



