Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአጋር ተቋማት ጋር ያዘጋጀው አራተኛው ዙር የኢንስቲትዩቱና አጋር ተቋማት ፎረምበዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሄደ፡፡

CERPHI

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአጋር ተቋማት ጋር ያዘጋጀው አራተኛው ዙር የኢንስቲትዩቱና አጋር ተቋማት ፎረምበዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሄደ፡፡ ፎረሙ የህብረት ስራን መጠናከር፣ ንቁ ተሳትፎን ማበረታታት እና የተቋማት የማያቋርጥ ድጋፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚከናወኑ የህብረተሰብ ጤና ስራዎች ውጤታማነት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡

ዶ/ር መሳይ ሀይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ወረርሽኝን በተሳካ ሁኔታ በመቆጣጠር ከበሽታው ነፃ መሆኗን አውስተው ይህም ትልቅ የህብረተሰብ ጤና ስኬት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ዶ/ር መሳይ አይይዘውም ይህ ስኬት ፈጣን የተጋላጭ ጉዳዮችን መለየት፣ የተቀናጀ የአደጋ ምላሽ ስርዓት፣ ጠንካራ የላቦራቶሪ አቅም፣ ውጤታማ የምርመራ እና የክትትል ስርዓቶች እንዲሁም የአጋር ድርጅቶች ጠንካራ ድጋፍ እና በሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ የተመራ አፈጻጸም ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ይህ ስኬት የተቋሙን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ጥንካሬን፣ የሰራተኞች ቁርጠኝነትና ብርታትን እንዲሁም የተቋማዊ ቅንጅት ውጤታማነት እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል፡፡ ዶ/ር መሳይ በዚህ አጋጣሚ አጋር ተቋማት እቅዶቻቸውን ከኢንስቲትዩቱ የስትራቴጂ ዕቅድ ጋር በማጣጣም ስራዎችን እንዲያጠናክሩ፣ የጋራ ክትትልና ግምገማ ስርዓቶችን እንዲያበረታቱ እና የአቅም ግንባታ ሰስራዎቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ሲ. ካሶሎ የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ህብረት ተወካይ በበኩላቸው የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያን የህብረተሰብን ጤና የአደጋ መቆጣጠርያ ማዕከላትን ለማጠናከር ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ዶ/ር ካሶሎ አያይዘውም እየተከናወነ ላሉት ልዩ ልዩ ስራዎች እገዛ እንዲሆን በአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድኖችን ማደራጀት፣ አስፈላጊ የሆኑ መድሀኒቶችና የግብዓት እቃዎች ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም የክትትል መረጃ ጥራትን ማሻሻል ስራዎች ላይ እና የመነሻ ፋይናንስ ድጋፍ መስጠት ላይ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ካሶሎ በተጨማሪም እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ይበልጥ ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር የተቀናጀና ውጤታማ ድጋፍ እንዲደርስ ድርጅቱ ሚናውን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በቢል እና ጌትስ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሹስና ዲ በበኩላቸው ተቋማቸው ኢንስቲትዩቱን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ዶ/ር ሹሲና የኢንስቲትዩቱን የቅርብ ጊዜ ስኬት በማውሳት ለማርበርግ ወረርሽኝ የተሰጠውን ምላሽ፣ የህብረተሰብ ጤና ደህንነት ማጠናከር መቻል፤ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል የሚረዱ ስርዓቶችን በተቀናጀ ትብብር መንፈስ መስራትና የተቀናጀ አመራር ምን ያህል ውጤታማነትን ማምጣት እንደሚቻል አመላክቶናል ብለዋል፡፡

በፎረሙ ላይ በዓለም ጤና ድርጅት እና ሪዞልቭ ቱ ሴቭ ላይቭስ በኩል የተከናወኑ ስራዎች ቀርበው ውይይቶች ተካሂዶባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ ሁሉም አጋር ድርጅቶች የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚያከናውናቸው ልዩ ልዩ ስራዎች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና ለሀገሪቷ ጠንካራና ተቋማዊ የህብረተሰብ ጤና ስርዓት ለመገንባት እየተደረገ ላለው ጥረት የበኩላቸውን ለማድረግቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *