
ሆሳዕና፤መጋቢት፣17/07/18 ዓ/ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከመጋቢት 18 እስከ 21/ 2018 ዓ/ም የሚሰጠዉን የአምስተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ አስመልከቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ እና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ መግለጫዉን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ከ1 ነጥብ አራት ሚሊየን በላይ ህፃናት የፖሊዮ ክትባት እንደሚከተቡ ገልጸዋል ፡፡
በ5ኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ከመጋቢት 18 እስከ 21/2018 ዓ/ም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በቤት ለቤት ጉብኝት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል ፡፡
ምክትል ሀላፊው አክለዉም የጤና አገልግሎት ለሁሉም በፍትሀዊነት ተደራሽ ለማድረግ ከፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ጎን ለጎን የቆልማማ እግር ልየታ፣ በመደበኛ ክትባት ያልወሰደ ህፃናትንና በተለያዩ ምክንያት ያቋረጡትን በመለየት ክትባቱን እንዲያገኙ ማድረግ ፣በተፈጥሮ አካል ጉዳት የደረሰባቸዉን ህፃናት በመለየት የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
በዘመቻው ወቅት የሴቶችና ህፃናት፣ የትምህርት ተቋማት ፣የሀይማኖት ተቋማት ፣የሚዲያ አካላት እና ሌሎች በዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት በዘመቻዉ ተሳታፊ ስለመሆናቸው አመላክተዋል።
አቶ አሸናፊ በየደረጃዉ የሚገኙ አመራርና ባለድርሻ አካላት ለተግባሩ ባለቤት ሆነዉ በቅንጅት በመስራት ለክትባቱ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ።
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው በክልሉ በሁሉሞ መዋቅሮች ከመጋቢት 18/2018 ዓ/ም ጀምሮ እድሜያቸዉ 5 ዓመት እና ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ለአራት ተከታታይ ቀናት ቤት ለቤት የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
ህፃናት ለፖሊዮ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በሽታዉ በንፅህና ጉድለት የሚተላለፍ ስለመሆኑ የጠቆሙት አቶ ማሙሽ ህብረተሰቡ የግልና የአካባቢው ንጽህና በአግባቡ እንዲጠብቅ የግንዛቤ ስራዎች በስፋት መስራት ይገባል ብለዋል።
የክትባት ዘመቻው ሲካሄድ የበሽታ ቅኝት ስራ ጎን ለጎን እንደሚሰራ የጠቆሙት አቶ ማሙሽ የስረዓተ-ምግብ ልየታ፣ ዜሮ ዶዝና ክትባት ያቋረጡ ህፃናት መለየትና በመከተብ እንዲሁም የቆልማማ እግር ችግር ያለባቸው በመለየት ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል።
በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የተቀናጀ የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በጥራትና በጥንቃቄ ተደራሽ ለማድረግ ግብዓትን ጨምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን አቶ አሸናፊ ገልፀዋል ፡፡
በመጨረሻም ወላጆች አሳዳጊዎች፣የሚዲያ አካላት፣ በየደረጃዉ የሚገኙ አመራር እና ማህበረሰቡ ለክትባት ዘመቻው ውጤታማነት የላቀ ሚና ስላላቸዉ ተግባሩን በባለቤትነት እና በተጠያቂነት መወጣት እንደሚገባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።የክልሉ ጤና ቢሮ፤

