
ቢሮው በጤናውን ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።
የቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንዳሉት ለጠንካራ የጤና ስርዓት ግንባታ የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር ወሳኝ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለጤና ተቋማት ግብዓት የሟሟላት ስራ መሠራቱንና ከመንግስት ድጋፍ በተጨማሪ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የግንባታና ግብዓት የሟሟላት ስራ በየአካባቢው እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመድሀኒት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ 31 የማህበረሰብ ፋርማሲን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ጠቁመዉ ተጨማሪ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ 25 ፋርማሲዎችን በቅርቡ በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በክልሉ የወባ፣የኩፍኝና ሌሎች ወረርሽኞችን መቀነስ መቻሉን ያመለከቱት አቶ ሳሙኤል በአጎራባች ክልል ተከስቶ የነበረው የማርበርግ በሽታ ወደ ክልሉ እንዳይዛመት ጠንካራ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት 85 በመቶው የእናቶች ማቆያ ያላቸው መሆኑን አስታውሰው የግብዓት ውስንነቶችን በመቅረፍ ምቹ የመቆያ ማዕከላት ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
89 በመቶ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ በመደረጉ በክልሉ የእናቶችና ህፃናት ሞት መቀነሱን የገለፁት አቶ ሳሙኤል እናቶች ሙሉ በሙሉ በጤና ተቋም እንዲወልዱ አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጤና የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ አሁንም ሰፊ ስራ የሚጠበቅ ነው ያሉት ሀላፊው የአመራሩ ፣የባለሞያዎችና የህብረተሰቡ ትጋት አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው ዋሌራ በበኩላቸው ቢሮው ከተቋም ግንባት ባለፈ ለህብረተሰቡ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የማህበረሰብ መሠረት የሆኑት እናቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በልዩ ትኩረት ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ገልፀው ውጤቱም አበረታች ነው ብለዋል።
የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግር የሆነው የመድሀኒት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተጀመረው የማህበረሰብ ፋርማሲ ግንባታ መጠናከር እንደሚገባው አስታውቀዋል።
ማህበረሰቡ የራሱ ጤና ባለቤት መሆን አለበት ያሉት አቶ ግዛቸው የገጠርና የከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ተግባራትን ማስፋት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የጤና መሠረተ ልማት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ በመሆኑ ማህበረሰቡን መሠረት ያደረገ የጤና ፋይናንስ ስርዓት ግንባታ ላይ ትኩረት መደረግ እንደሚገባው ገልፀዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የጤናው ስርዓት የህብረተሰቡን እርካታ ያረጋገጠ ለውጫዊና ውስጣዊ ወረርሽኞችን ምላሽ ሰጪ እንዲሆን የባለሞያዎችን አቅም በማሳደግ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓቱን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።






