
መጋቢት 08/2018 ዓ.ም – ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ግብርና ኮሙኒኬሽን
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእንስሳት ጤና ጥበቃ ሥርዓቱን ለማሻሻል ያለመ የዘርፈ ብዙ ባለሙያዎች የአንድ ጤና ጽንሰ-ሀሰብ (Multisectoral One Health) የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
መድረኩ በብሔራዊ የውሻ አብደት በሽታ ክትትል፣ መከላከልና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ እንዲሁም በክልል አፋጣኝ ምላሽ ሰጪ ቡድን (Regional Rapid Response Team) ምስረታ ላይ ያተኮረ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር የሥልጠናውን መድረክ ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት ባለፉት ሰባት ዓመታት ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግና የድህነትን ታሪክ ለመቀየር በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የድህነትን ታሪክ ለመቀየር የእንስሳትና ዓሳ ዘርፍ ትልቁን ስፍራ ይይዛል ያሉት ኃላፊው የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ ኢኒሼቲቭ የሆነው የሌማት ትሩፋት መርሃግብር ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
በተለይም ጸጋዎቻችንን አልምተን መጠቀም የምንለው ጉዳይ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ በተጨባጭ ማየት ጀምረናል ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፉት 3 ዓመታት ዝርያ ለማሻሻል በተሰራው ሥራ በክልሉ 8 የወተት ማማቀነባበሪያ ኢንደስትሪዎችን አርሶአደሮችን በህብረት ሥራ በማደራጀት የማይቻል የሚመስለውን እንዲቻል መደረጉን አቶ ኡስማን ጠቁመዋል።
የዘርፉን ምርታማነት በቀጣይነት ለማሳደግም የተቀናጀና የተሳለጠ የአንድ ጤና አጠባበቅ ሥርዓት የጎላ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ሥልጠናውየእንስሳትን ጤናን ከመጠበቅ ባለፈ ድንገተኛ የበሽታ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ወቅት በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚችል የባለሙያዎች ቡድን (Regional Rapid Response Team) ለማቋቋም ያለመ ነው።
ይህም የዘርፉን ምርት በጥራት በማምረት የውጭ ኤክስፖርትን ለማሳደግና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል ሲሉ አቶ ኡስማን በመድረኩ ገልጸዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ የእንስሳት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ጋሼ በበኩላቸው ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን በቅንጅት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ የእንስሳት ውጤቶችን ለህብረተቡ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጤና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ወደ ውጪ በሚላኩ የእንስሳት ውጤቶች ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ የሰው፣ የአካባቢ ጥበቃና የእንስሳት ጤናን በቅንጅት በመከላከል መስራት ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ከዓለም አቀፍ ምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ መድረክ ላይ ከክልል፣ ከዞን፣ ከልዩ ወረዳ፣ ከወረዳና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የእንስሳት ጤና፣ የድንገተኛ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።



