
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ አመት አፈጻጸም ግምገማ በሀላባ ቁሊቶ እያካሄደ ይገኛል፡፡
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት ማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ እንደ ክልል በሕብረተሰብ ጤና ዙሪያ በተተገበሩ ተግባራት ኢንስቲትዩቱ ያስቀመጣቸው ራዕይ፣ ተልዕኮ እና ግቦች ለመፈጸም በቁርጠኝነት አየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመጡ ተላላፊ በሽታዎች፣ የአየር ንብረት ጋር የተያያዙ የጤና ቀውሶችና፣ በቅርብ ጊዜ የተከሰቱት ዓለም ዐቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን ለወረርሽኝ የማይበገር የጤና ስርዓት በመገንባት ጠንካራ የቅኝት እና ምላሽ ስራዎችን በመስራት መመከት መቻሉንም አቶ ማሙሽ ገልጸዋል።
ጥራት ያለው የተናበበና ታዓማኒነቱ የተረጋገጠ የመረጃ ስርዓቱን ወቅቱን በሚመጥንና ዘመኑን በዋጀ መልኩ በማዘመን በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥ ባህልን ማዳበር መቻሉን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ
ዓለም ዓቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ጠንካራ የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶች፣ ፈጠራዎችና ምርምሮች እንዲሁም ቀልጣፋ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ስርዓት ለድንገተኛ አደጋዎች የሚሰጡ የምላሽ ስራዎችን ለማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
ባለፉት 6 ወራቶች የወረርሽኞችን አሰሳና ቅኝትን ለማጠናከር፣ የማህበረሰብን ግንዛቤ ይበልጥ ለማሻሻልና ከአጎራባች ክልሎች ጋርም በቅንጅት ሲሰራ መቆነቱን ያመላከቱት አቶ ማሙሽ በክልሉ በበጀት ዓመቱ ወረርሽኝ እና ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ማለትም በወባ፤ በኩፍኝ እና በኮሌራ የነበረውን ጫና በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
የጤና አገልግሎቶችን በጥራትና በፍትሃዊነት ተደራሽነት በምርምርና ቴክኖሎጂ ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራቶች እየተፈጸሙ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ለችግሮች መፍትሔ የሚያመጡ 8 የምርምር ጥናቶችን ለዓለም አቀፍ ጆርናሎች በመላክ 5ቱ ለህትመት ተቀባይነት አግኝተው የመጨረሻው የህትመት ምዕራፍ ላይ እንዲደርሱ መደረጉን እንዲሁም ሌሎች 7 የሚጠጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች በሂደት ላይ የሚገኙ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
የሀላባ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ሸምሱ ረሺድ በበኩላቸው በድንገት የሚከሰቱ ወረርሽኞችንና በተፈጥሮ አደጋ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ የጤና ቀውሶች በማህረሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት የተቀናጀ የቅኝትና የምላሽ ስራ በመስራት የህረተሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ርብርብ መደረጉን ገልጸዋል ፡፡
በዝናሽ ደለለኝ








