
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከኑትሪሽን ኢንተርናሽናል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጆኤል ስፔንሰር ጋር በኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ፕሮግራሞችን ለማጠናከር እና የዘርፈ ብዙ ትብብርን ለማሳደግ ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ዶ/ር መቅደስ በስርዓተ-ምግብ ፕሮግራሞች ተጽዕኖን በማሳደግ ለመምራት እና ለማፋጠን ተጨባጭ እና አስተማማኝ መረጃ ማመንጨት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል። የስርዓተ ምግብ መዛባት ችግርን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፍታት እና ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች ከፍተኛ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ተግባራትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ዘርፎች መካከል የተጠናከረ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር መቅደስ፣ ስርዓተ-ምግብ የጤና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በግብርና፣ በትምህርት፣ በውሃ፤ በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የተቀናጀ ጥረትን ይጠይቃል ብለዋል።
ስርዓተ-ምግብ እና የሕጻናት ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ በሰቆጣ ቃል ኪዳን በሁሉም ክልሎች 520 ወረዳዎች የብዝሀ ሴክተር ትግበራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው በጤና ዘርፍም ቁልፍ አጀንዳ በማድረግ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በመተግበር ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ጆኤል ስፔንሰር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በምታከናውናቸው የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ተግባራት ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች አድንቀው የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ አገሪቱ የስርዓተ ምግብ ትግበራን ውጤቶች በማሻሻል እና በተቀናጀ መልኩ በማስተባበር በመተግበሯ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቧን ገልጸዋል፡፡
ድርጅታቸው መንግስት የስርዓተ-ምግብ እና የሕጻናት ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ ለሚተገብራቸው ተግባራት የበኩሉን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ሌሎችንም አካላት በማስተባበር ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
Website: moh.gov.et
Facebook: Ministry of Health,Ethiopia
Twitter: x.com/fmohealth
YouTube: youtube.com/@FMoHealthEthiopia
Tiktok: tiktok.com/@mohethiopia
Telegram: t.me/M0H_EThiopia
Linkedin: lnkd.in/ewFJ6VAB



