
(ሆሳዕና፦ የካቲት 6 /2018) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ላይ በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሀላባ ቁሊቶ ከተማ መክሯል።
የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እንደገለፁት የክልሉ ጤና ኢኒስቲትዩት በህብረተሰቡ ጤና አጠባበቅ ላይ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል እያከናወነም ይገኛል ብለዋል።
የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ጠንካራ የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶች፣ ፈጠራዎችና ምርምሮች እንዲሁም ቀልጣፋ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ስርዓት ለድንገተኛ አደጋዎች በሚሰጠው የምላሽ አቅም የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክረው ይቀጥላል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት የወረርሽኞችን አሰሳና ቅኝትን ለማጠናከር፣ የማህበረሰብን ግንዛቤ ይበልጥ ለማሻሻልና ከአጎራባች ክልሎች ጋር ቅንጅታዊ አሰራሮችን ለማጠናከር በተደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
በተለያዩ ክልሎች የተከሰተው የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ወረርሽኝ ወደ ክልላችን እንዳይገባ በተለይም ከ20ኛው የብ/ብ/ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር ጋር በነበረው ቅድመ ዝግጅትና ድህረ ዝግጅት በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ ክልሉን ከወረርሽኝ ስጋት ነፃ ለማድረግ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ማለትም በወባ፤ በኩፍኝ እና በኮሌራ የነበረው ጫና በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ የተቻለ ሲሆን የምላሽ አቅሙም እንደ ክልል ከጊዜ ወደ እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል።
በዘርፉ መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች በማሻሻል ለቀጣይ ተግዳሮቶችን በመለየት የክልሉ ህብረተሰብ ጤናን በማስጠበቅ ተግባር ላይ የጋራ ኃላፊነትን ለመወጣት መረባረብ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል ።
በክልሉ የተላላፊ በሽታዎችን ቅኝትና የአደጋ ቅድመ ዝግጁነትን ማጎልበት በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ለውጥ ታይቷል።የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመጠቀም የወረርሽኝ ቁጥጥርና የአስተዳደር ስርዓት የቅኝት ስራን በማጠናከር፣ፈጣን ምላሽ በመስጠት፣ የቅንጅትና የትብብር ስራን ማጎልበት ያስፈልጋል ተብሏል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቅንጅት በተሰሩ ተግባራት በጤናው ዘርፍ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ ስለመምጣታቸው ተናግረዋል።
በቀጣይ ተላላፊ እና በሌሎች ወረርሽኝ በሽታዎች ላይ በቁርጠኝነት በመስራት በህብረተሰቡ ጤና አጠባበቅ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጠት እንደሚረባረቡ ተናግረዋል።
በመድረኩም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው ዋሌራን ጨምሮ የክልል፣የዞንና ልዩ ወረዳዎች ባለድርሻ ተገኝተዋል።
በእለቱም የተለያዩ የጥናት ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን በክልሉ የማርበርግ ቫይረስ መከላከል ላይ አስተዋጾኦ ላበረከቱ መዋቅሮችና ተቋማት የምስክር ወረቀትና እውቅና የመስጠት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በአድነው አሰፋ
ለተጨማሪ መረጃ ![]()
በዌብሳይት https://www.cergcab.et/
በቴሌግራም https://t.me/CERGCAB
በፌስቡክ https://www.facebook.com/profile.php?id=100070605291100&mibextid=ZbWKwL
በቲውተር https://twitter.com/CabCerg2678
በቲክቶክ tiktok.com/@cerg2225
በዩቲዩብ https://youtube.com/@centralethiopiacommunication…
በኢንስታግራም https://www.instagram.com/cergcab/profilecard/?igsh=MWNseXBlaW05dnM3MA==
ምርጫችሁ ስላደረጋችሁን እናመሰግናለን !!
















