
በጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የተመራዉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ቡድን በነቀምቴና አካባቢው የሚገኙ ጤና ተቋማትን ጎብኝተዋል።
___________
ይህ ጉብኝት ኅብረተሰቡ እያገኘ ያለውን የጤና አገልግሎት ጥራትና የተቋማቱን አጠቃላይ ቁመና በአካል ተገኝቶ ለመገምገም ታላቅ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየትና ተግዳሮቶችን በቅርበት በመረዳት ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ልዑካን ቡድኑ በቆይታው የዞኑን መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት፣ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልንና በግንባታ ላይ የሚገኙ የተማሪዎች ማደሪያ ሕንጻዎችን፣ በኬ ጃማ ጤና ጣቢያ፣ የነቀምቴ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ሪፈራል ላቦራቶሪና የሕብረተሰብ ጤና ምርምር ማዕከል እና ሌሎች የልማ ተመልክቷል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ በተቋማቱ ተገኝተው የእናቶችና ሕፃናት ሕክምናን፣ የመድኃኒት አቅርቦትን የድንገተኛ አደጋ፣የላቦራቶሪና የሪፈራል የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን ተመልክተው በተቋማቱ የሚታዩ የአገልግሎት ክፍተቶችንና መሠረታዊ ተግዳሮቶችን በውል ለመለየት ያስቻለ ሲሆን፣ በተለይም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የሕክምና ዘርፎች ለማጠናከር የሚያስችል ግብዓት የተገኘበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመጨረሻም በተጎበኙ የጤና ተቋማትና በዞኑ በተለዩ የአገልግሎት ክፍተቶች ዙሪያ ማሻሻያዎችን ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ከሆኑት ከአቶ መስፍን መላኩ ጋር ውይይት ተደርጓል።
ይህ የጋራ ውይይት በዞኑ የሚታዩ የጤና ዘርፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩም ተመላክቷል።
Website: moh.gov.et
Facebook: Ministry of Health,Ethiopia
Twitter: x.com/fmohealth
YouTube: youtube.com/@FMoHealthEthiopia
Tiktok: tiktok.com/@mohethiopia
Telegram: t.me/M0H_EThiopia
Linkedin: lnkd.in/ewFJ6VAB
