
በዓለም አቀፍ የላቦራቶሪ የጥራት መስፈርቶች (ISO 15189፡2022 Standards) ትግበራ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ጥር 28/2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥልጠና ማእከል በተሳካ ሁኔታ ተሰጥቷል:: በዚህም መድረክ በISO 15189፡2022 መስፈርቶች አክሬዲቴሽን እና በSLMTA የትግበራ መርሃ-ግብሮች ላይ እየተሳተፉ ካሉ የተለያዩ ጤና ተቋማት የተጋበዙ የበላይ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መለሰ እንደገለጹት የላቦራቶሪ ጥራት በተለይም በዓለም አቀፍ የላቦራቶሪ ጥራት መስፈርቶች (ISO 15189፡2022 Standards) ትግበራ ላይ ውጤት ለማምጣት በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማት የበላይ ኃላፊዎች የመሪነት ሚና፣ ቁርጠኝነት እና የባለድርሻ አካለት ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እና ይህ የግንዛቤ ማስጫበጫ መድረክም በ2018 ዓ.ም የበጀት ዓመት የላቦራቶሪ ጥራት ትግበራ መርሃ ግብር ውስጥ የተካተቱ ሆስፒታሎች ያሉበትን ደረጃ መገምገም እና በቀጣይ ስድስት ወራትም ያላለቁ ስራዎችን በመጨረስ በውጤት ለማጠናቀቅ በሚሰፈልጉ ስራዎች ላይ ውይይት ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸው በተጨማሪም በዚህ ዘርፍ ቀድመው ውጤት ባስመዘገቡ ተቋማት የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት አሰጣጥ በመሻሻሉ የተገልጋዮች እርካታ በእጅጉ መጨመሩን እና ለዚህም ውጤት የተቋማትን ኃላፊዎች እና የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን አመስግነዋል።
ተሳታፊዎች በየተቋሞቻቸው የላቦራቶሪ የጥራት ስታንዳርድ ትግበራ ላይ ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶችን አስመልክቶ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ ቀድመው በዚህ ዘርፍ ውጤት ያመጡ ተቋማትም ተሞክሯቸውን አጋርተዋል፡፡
በሥልጠናው መጨረሻ ላይም በተነሱ ለተለያዩ ጥያቄች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፤ በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ ለዚህ ትግበራ የተለዩ ተቋማት ዓለም አቀፍ የላቦራቶሪ ጥራት መስፈርቶች ላይ እውቅና እንዲያገኙ ኃላፊዎች የሚጠበቅባቸውን ከፍተኛ ሚና እንዲወጡ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፣ ለዚህም መሳካት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም አስፈገላጊውን ድጋፍ እና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከመድረኩ ለመረዳት ተችሏል፡፡



