
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል “ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ቃል የጤናማ እናትነት ወር በቡታጅራ ጠቅላላ ሆስፒታል እየተከበረ ይገኛል ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የእለቱን ፕሮግራም ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት የጤናማ እናትነት ወርን ለእናቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በላቀ ደረጃ ተደራሽ በማድረግ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የሚሰራበት መሆኑን ተናግረዋል ።
በሀገር ደረጃ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ከአስር ሺህ እናቶች 871 ይሞቱ ከነበረበት ወደ 141 መቀነስ መቻሉን የጠቆሙት አቶ ሳሙኤል ይህንንም ቁጥር በ2030 ወደ 70 ለማድረስ ለተያዘው ዕቅድ መሳካት ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በክልሉ የእናቶችን ሞት ቅነሳ ላይ በርካታ ዉጤታማ ስራዎች በመሰራቱ አበረታች ዉጤት መመዝገቡን አቶ ሳሙኤል አንስተዋል ።
እናቶች ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ አገልግሎት ላይ በትኩረት በመሰራቱ በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መሻሻሉን ሀላፊዉ ገልፀዋል።
እናቶች ፈጥነዉ ወደ ህክምና ተቋም እንዲደርሱ እና በትራንስፓርት ችግር እንዳይሞቱ ባለፉት ዓመታት ከ200 በላይ አምቡላንስ ተደራሽ መደረጉን አቶ ሳሙኤል ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡን በማስተባበር ለእናቶች ጤና አገልግሎት የሚውሉ ሀብቶችን በማሰባሰብ የጤና ተቋማትን በግብዓት የማሟላት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል ፡፡
የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በክልሉ ምቹ የሆነ የነብሰ ጡር እናቶች ማረፊያ ቤት በየጤና ተቋማት በመገንባት ከሌሎች ክልሎች በአንፃራዊ የተሻለ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አቶ ሳሙኤል በክልሉ የእናቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎትን ለማሳደግ በቀጣይ በዘርፉ የሚከናወኑ ስራዎችን በቅንጅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል ።
የቡታጅራ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቶፊቅ ሙሳ በበኩላቸው ሆስፒታሉ የእናቶችን እና የህጻናትን ጤና በመጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸው የጤናማ እናትነት ወር የግንዛቤ የማስጨበጫ በሆስፒታሉ መደረጉ በእናቶች ላይ የሚሰራውን ስራ ይበልጥ ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል ።
በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕረዝዳንት ልዩ አማካሪ እና ረዳት ዶ/ር ንጉሴ አስረስ፣የጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊዎች ፣ የክልሉ ሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ነጅሚያ ራመቶ፣የቢሮዉ የማነጅመንት አካላት፣የዞን እና ልዩ ወረዳ ጤና ኃላፊዎች ፣ የቡታጅራ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኬያጅ አቶ ቶፊቅ ሞሳ ፣ አጋር አካላት እና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል። ሸምሲያ አደም
1/6/18ዓ/ም ወራቤ






