
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮየ “ጠንካራ የአመራር ግንባታ ለውጤታማ የጤና ስርዓት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ስልጠና በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ እየተሰጠ ይገኛል በዚህም ከክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የተወጣጡ የጤናዉ ዘርፍ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ፡-የጤናዉ ዘርፍ አመራር በአካባቢ የሚገኙ ፀጋዎችን በመጠቀም ፣ ማህበረሰቡን በማስተባበር በሴክተሩ እመርታዊ ለዉጥ እንዲመዘገብ ተግቶ መስራት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ 2030 የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን እያደረገችዉ ያለዉን ሁሉ አቀፍ ጥረት እዉን ለማድረግ የጤናዉ ዘርፍ አመራር የራሱን ሚና መጫወት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከተረጂነት በመውጣት በራስ አቅም ጤናማና አምራች ዜጎችን ለመፍጠር ከተረጂነት የወጣ እሳቤን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
እንዲሁም በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎትን በማስፋት በዘርፉ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ዉስንነቶችን ለመቅረፍ የተጀመረውን ጥረት ማገዝ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
በተለይም የጤና ተቋማትን ደረጃ የማሻሻል የተሟላ ግብዓት በማቅረብ የተሟላ የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ በማቅረብ ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር እየተደረገ ያለዉን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የአቅም ግንባታ ስልጠናውን ሲያስጀምሩ እንዳስታወቁት ውጤታማነትንና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረጉ የጤና ልማት ስራዎች በክልሉ ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው።
ዘላቂነት ያላቸው፣በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች በቀላሉ የማይበገር የጤና ስርዓት ለመዘርጋት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ቢሮ ሃላፊው አመላክተው፤ለስራዎቹ ስኬት የአመራሩና የፈጻሚው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አሳውቀዋል።
የአቅም ግንባታ ስልጠናው የተጠናከረ የጤና ስርዓት መፍጠር ላይ ያተኮረ ስለመሆኑም ያብራሩት አቶ ሳሙኤል ፣ባለቤትነትን መፍጠርና ከዚያም ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በክልሉ የጤናውን ዘርፍ ለማሻገር ተግዳሮት የሆኑ 15 ጉዳዮች በሳይንሳዊ ጥናት መለየታቸውንና ተግዳሮቶቹን ለመፍታትም 12 ስትራቴጂካዊ መፍትሄዎች በጥናቱ መቅረባቸውንም ገልጸዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ሀይሶ ዩኒቨርሲቲዉ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎትና በሰው ኃይል ልማት በቅንጅት ለመስራት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ስልጠና ውጤታማ ተቋማዊ አሰራርን ለመዘርጋት፣ ውስን ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀምና በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ትልቅ አቅም ሲሉም ተናግ።
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ስልጠና መሳካት አስፈላጊውን ግብዓትና ምቹ መስተንግዶ ለማቅረብ ሙሉ ዝግጅት አድርጓል ያሉት ፕሬዝደንቱ ናቸው።
በቢሮዉ ለተከታታይ 7 ቀናት በሚሰጠዉ የግንዛቤ ስልጠና መርሃ ግብር ላይ ከተለያዩ የወረዳ መዋቅር የተዉጣጡ ከ175 በላይ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በአቅም ግንባታ የስልጠና መድረኩ የክልሉ ጤና ቢሮ የስራ ሃላፊዎች፣የማኔጅመንት አባላትና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።



