Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በምስራቅ ጉራጌ ዞን የቡኢ ከተማ አስተዳደር ጤና ጣቢያ በመመረቅ አገልግሎት አስጀመሩ ፡

ጤና ጣቢያ ምረቃው የክልል ፣ የዞን፣ የወረዳና የቡኢ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፤ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ በተገኙበት ተመርቆ ስራ ጀምሯዋል።

በምርቃ ስነ ስረዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንደተናገሩት፣ በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋፋት የህዝቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ጤና ጣቢያው የህዝብና የአመራር ቅንጅትና ትብብር የታየበት መሆኑን ያነሱት የቢሮ ኃላፊው፣ በጤና ጣቢያ ደረጃ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን በመስጠት ሞዴል ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

በዚህ ደረጃ የሚሰጡ ሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎቶችን በመስጠት የጤና ባለሙያዎች ሌት ተቀን ያለመታከት ሊሰሩ ይገባል ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ ክልሉ የግብዓትና የቴክኒካል ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሱ አበጋዝ በበኩላቸው የዞኑ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ጤና ጣቢያ ግንባታ ህዝቡን በማስተባበር መሰራቱ አንስተው የዚህ ውጤት በከተማው ሌሎች ልማቶችን ለመስራት ልምድ የሚሰጥ መሆኑንም አንስተዋል ፡፡

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፣ በሽታን ቀድሞ ከመከላከል ጎን ለጎን አክሞ ለማዳን በርካታ የጤና አገልግሎት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በዚህ ረገድም ህዝብን በማስተባበር የጤና ተቋማትን በመገንባትና ግበዓት በማሟላት የጤና አገልገሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የቡኢ ከተማ አስተዳደር ገና ታዳጊ ከተማ ቢሆንም ህዝብን በማስተባበር ይህን ጤና ጣቢያ መገንባት መቻሉ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የማጠናቀቅ ቃልን በተግባር አይነተኛ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

የቡኢ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ በለጠ ጫካ በበኩላቸው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ በተፈጠረ የልማት ተነሳሽነትና በአመራሩ ቁርጠኝነት ጤና ጣቢያውን ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ተናግረዋል።

የከተማው ነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት ከንቲባው፣ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ፍላጎቶችን ለሟሟላት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም የጤና አገልግሎት ሽፋን ከማሳደግ አኳያ ጤና ጣቢያው የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ መሆኑን ጠቁመው፣ ለጤና ጣቢያው ግንባታ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ወጪ መደረጉንም ተናግረዋል።

በዕለቱ የክልሉ ጤና ቢሮ አመራሮች የቡዒ ከተማ አስተዳደር የማህበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አኑረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *