
በአፈጻጸም ግምገማው ሁሉም ዳይሬክቶሬቶች አፈጻጸማቸውን አቅርበው ውይይት ተካሂዷል ፡፡
በክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በመድረኩ እንደገለጹት ባለፉት 6 ወራት በኢኒስቲትዩቱ የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም አበረታች እና ውጤታማ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ የተሻለ ለመፈጸም የሚያነሳሳ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው የጤና አገልግሎት ስርዓቱን በመገንባት በድንገት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በአፋጣኝ በመመከት የማህበረሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚሰጠው የላብራቶሪ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ እና የላብራቶሪ አገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው ያሉት አቶ ማሙሽ መደበኛ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን በጥራት ለመፈጸም ያስችላል ብለዋል።
የላብራቶሪ መረጃ አያያዝ አደረጃጀት አጠቃቀም እንዲሁም አሰተዳደር ስርዓቱን በማሳለጥ ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የጤና ምርምር ስራዎች ውጤት አምጪ እና የማህበረቡን የጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የሚጠቅሙ እንዲሆኑ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ፣ የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ላቦራቶሪ፣ የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የጤና ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬቶች የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈጻጸም ሪፖርቶች ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ የኢኒስቲትዩቱ ዳይሬክተሮችና አጠቃላይ ባለሙያዎች በተገኙበት በቢሮ ደረጃ የአፈጻጸም ግምገማ መካሄዱም ታውቋል።


