
ስልጠናው በጤና ተቋማት ውስጥ የተገልጋዮች እርካታ መጠን ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመለየት ያለመ እንደሆነ ተመላክቷል።
ሰልጣኞቹ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከሶስቱም ዩኒቨርሲቲዎች (ከዋቸሞ፣ ከወራቤና ወልቂጤ) እንዲሁም ከሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተውጣጡ ተመራማሪዎችና መምህራን ናቸው።
በክልሉ ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የተገልጋዮች እርካታ መጠን ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት የቀጣይ መፍትሔ አቅጣጫ ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ስልጠና እንደሆነ ተናግረዋል።
አቶ ማሙሽ፦ የጤና መረጃ ሰብሳቢዎች መረጃዎችን በጥንቃቄ በመሰብሰብ በታሰበው ቀንና ጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ እንዳለባቸው አስተውቀዋል።
የሚሰበሰቡ የጤና መረጃዎች ተዓማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ የሚሰጡ አጋዥ ሥልጠናዎችን በአግባቡ መከታተል እንዳለባቸውም ለጤና መረጃ ሰብሳቢዎች መልዕክት አስተላልፈዋል አቶ ማሙሽ።
በክልሉ ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ከላዬ በበኩላቸው የጤና መረጃ ለማዘመንና የተገልጋዮችን እርካታ መጠን ለማሳደግ በእቅድ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ጥራቱ የተጠበቀ የጤና መረጃ በጤናው ዘርፍ ለሚደረገው ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ በመሆኑ ለሥራው ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።
ሰልጣነኞች በሰጡት አስተያየት፦ የክልሉ ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስልጠናውን እድል በማመቻቸቱ አመስግነዋል።
ቀጣይ በሚሰማሩባቸው መደበኛ የጤና ስራዎች ላይ ውጤታማ ተግባር ማከናወን እንዲችሉ የስልጠናው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም አንስተዋል።
በአብርሃም ሙጎ


