
በሀገራችን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማርበርግ ቫይረስ በሽታ (Marburg Viral Disease) መከሰቱን ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ሕዳር 5 ቀን 2018 ዓ/ም ባወጣዉ ወቅታዊ መግለጫ ማሳወቃችን ይታወቃል፡፡
ከዚያም ዕለት ጀምሮ በጤና ሚኒስቴር የተቋቋመው ግብረሃይል ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከክልል የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር እና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ከሕብረተሰባችን ጋር በመተባበር ተሰርቷል።
በሽታውን በተመለከተም አዳዲስ መረጃዎችን በጤና ሚኒስትር ድህረ ገጾች ላይ በመደበኛነት ለህብረተሰቡ ሲያጋራም ቆይቷል።
በሀገራችን የመጀመሪያው የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ታማሚ ከተገኘበት እለት ጀምሮ እስከ ዛሬ ታህሳስ 27/2018 ዓ/ም ድረስ በአጠቃላይ በበሽታው ለተጠረጠሩ 38oo ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን 14ቱ የማርበርግ ቫይረስ እንደተገኘባቸውም ለማረጋገጥ ተችሏል።
ከእነዚህም ውስጥ ዘጠኙ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን አምስቱ ደግሞ ከበሽታው ማገገም ችለዋል፡፡
ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር እና የህብረተሰባችንን ጤና ለመጠበቅ የክስተት አስተዳደር ስርዓትን በመዘርጋት የተቀናጀ ቅኝትና ምላሽ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
ተንቀሳቃሽ እና ቋሚ የላቦራቶሪ ምርመራ የማደራጀት፥ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ወደቦታው የመላክ፥ የለይቶ ማቆያ እና ማከሚያ ማዕከላት የማቋቋም፤ የሚያስፈልጉ የሕክምና ግብአቶችና የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁሶችን የማሟላት፣ ለበሽታው መከላከያና ህክምና የሚውሉ መድሃኒቶችንና ክትባቶችን ወደሃገር ውስጥ የማስገባት ስራዎች በሰፊው ተሰርተዋል።
የቅኝትና የግንዛቤ ስራዎችን ከሀገር አቀፍ የፖሊዮ ዘመቻ ጋር በማቀናጀትም በዘመቻው ወቅት ከ20 ሚሊዮን በላይ አባ እማወራዎችን መድረስ ተችሏል።
በመውጫና መግቢያ ኬላዎች ልየታዎችን በማካሄድ ለ4.8 ሚሊዮን ተጓዦች ልየታ የተደረገ ሲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሕዝብ በዓላትን በጥንቃቄ እንዲከበሩ ከማድረግ አኳያም ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል።
ከሃይማኖት ተቋማት እና ከሚድያ አካላት ጋር በመተባበር ማህበረሰባችን ስለበሽታው ያለው ዕውቀት እንዲዳብር የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በሰፊው ተሰርተዋል።
በተጨማሪም የበሽታውን ምልክቶች ካሳዩ ወይም በላቦራቶሪ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር ንክኪ እና ተጋላጭነት ለነበራቸው 886 ሰዎች ክትትል እና የመከላከያ ህክምና ማድረግ ተችሏል።
ከመጨረሻዎቹ የማርበርግ ታካሚዎች ጋር ንክኪ ለነበራቸው 296 ሰዎችም ባለፉት 21 ቀናት የቅርብ ክትትል ሲደረግ ቆይቶ ሁሉም ክትትላቸዉን ጨርሰው ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ ችለዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሆኖ ባደረገው ርብርብና ያለሰለሰ ጥረት ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን፤ በዚህ ወረርሽኝ ምላሽ ላይ የተሳተፉ እና እየተሳተፉ ያሉ የጤና ባለሙያዎቻችን፣ የዘርፉ አመራሮች፣ አጋር አካላት እና ሁሉንም የሕብረተሰባችን ክፍል ከልብ ለማመስገን እንወዳለን።
በአለም ጤና ድርጅት (WHO) እንዲሁም በሃገራችን የማርበርግ በሽታ ቅኝት እና ምላሽ መመሪያ መሰረት ወረርሽኙ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉ የሚታወጀው የመጨረሻዉ የማርበርግ ታማሚ ከነበረበት 42 ቀናት ዉስጥ ሌላ ተጨማሪ በበሽታው የተያዘ እንዲሁም ህይወቱ ያለፈ ሰው አለመኖሩ ሲረጋገጥ ነው።
በዚህም መሰረት ባለፉት ሶስት ሳምንታት (21 ቀናት) በማርበርግ ቫይረስ በሽታ የተያዘ ወይም ምልክቶችን ያሳየ ሰው በሃገራችን ባለመገኘቱ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ከተረጋገጠ የማርበርግ ታማሚ ጋር ንክኪ ኖሮት ክትትል የሚደረግለት ሰው ባለመኖሩ፤ አሁንም ሳንዘናጋ እና ችላ ሳንል ከዚህ በፊት ስንተገብራቸው የነበሩትን የቅኝት ስራዎች፥ የማሕበረሰብ አቀፍ የበሽታ መከላከያ መንገዶችን እና የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦቶችን ለሚቀጥሉት ተጨማሪ 21 ቀናት በይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ሙሉ በሙሉ ለመግታት እና የህብተሰባችንን ጤና ለመጠበቅ የማህበረሰብ እና የባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ የሚከተሉትን ቁልፍ የህብረተሰብ ጤና ምላሽ ተግባራት ላይ በትኩረት የምንሰራ ይሆናል፦
• በማህበረሰብ እና በጤና ተቋማት ውስጥ የተጠናከረ የበሽታዎች ቅኝት እና ክትትልን ማካሄድ፣
· የበሽታው ምልክት የታየባቸውን ተጠርጣሪዎችን የመለየት፣ የማሳወቅ እና ቶሎ የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ፣
በሁሉም የጤና ተቋማት የበሽታውን ስርጭት የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራዎችን ማጠናከር፣
· በማህበረሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ አሉባልታዎች እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመግታት ቀጣይነት ያለው የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ስጋት ተግባቦትን እና የማህበረሰብ ተሳትፎን በየደረጃው ማጠናከር
ስለዚህም ማህበረሰባችን ሳይዘናጋ የበሽታውን ምልክቶች በንቃት በመከታተል እና ሪፖርት በማድረግ፥ ምልክቱን የሚያሳዩ ታማሚዎች ሲኖሩም ንክኪን መቀነስ፣ እጅን በውሃና በሳሙና ወይም በሳኒታይዘር ማጽዳት እና ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል።
በመጨረሻም በየደረጃው ካሉ የጤና ስርዓት መረጃዎችን መከታተል እንደሚያስፈልግ እየገለጽን ቀሪዎቹን 21 ቀናት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ እናሳስባለን።
ዶ/ር መቅደስ ዳባ
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር
ታህሳስ 27/2018
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
