Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የአእምሮ ጤና አገልግሎትን በድንገተኛና በከፍተኛ አደጋዎች ወቅት ተደራሽ እናድርግ!” በሚል መሪ ቃል የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን ተከበረ::

የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊዎችና የማናጅመንት አካላት የዞንና የልዩ ወረዳ ጤና መምሪያና ጽ/ቤት ኃላፊዎች የሆስፒታሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል “የአእምሮ ጤና አገልግሎትን በድንገተኛና በከፍተኛ አደጋዎች ወቅት ተደራሽ እናድርግ!”በሚል መሪ ቃል የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን በዛሬው ዕለት ተከብሯል።

አቶ ለገሰ ጴጥሮ የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይርክተር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የአእምሮ ጤና ቀን የሚከበርበት ዋና ዓላማ ስለ አእምሮ ጤና ግንዛቤ ማሳደግ እና በአእምሮ ጤና መታወክ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ እና ዘርፈ ብዙ እየሆነ በመምጣቱ፤ ችግሮቹ የሚሹትን ምላሽም እንዲሁ ዘርፈ ብዙ በመሆኑና የአእምሮ ጤና ችግር እያደረሰው ካለው ጫና አንፃር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚሰጡትን የምላሽ ስራ ማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።

ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ የኑሮ ሁኔታና የአየር ንብረት ለውጥ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚያባብሱ ከመሆናቸው ረገድ የአእምሮ ጤና አገልግሎትን በድንገተኛ እና በከፍተኛ አደጋዎች ወቅት ተደራሽ በማድረግ ቀውሱን ለማስቀረት ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የአእምሮ ጤና በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ እንዲሁም የጤና ቀውስ ለማስቀረት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመስራት ድንገተኛ የጤና አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ በየደረጃው ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ዶ/ር ካሊድ ሸረፋ የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ1992 እ.ኤ.አ የአእምሮ ጤና ቀን መከበር መጀመሩንና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ 34ኛ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበር መሆኑን በማስገንዘብ የአዕምሮ ጤና እክል በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል በመጠቆም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሆስፒታሉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

ሆስፒታላችን ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር ከአማኑኤል ሆስፒታል ቀጥሎ ፎረንሲክ ሳይካትሪ፣ በስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ አገልግሎት በመስጠት በተመላላሽ እና ተኝቶ ህክምና የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ያሉት ዶ/ር ካሊድ ናቸው።

በአማኑኤል ሆስፒታል እና በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ላይ የሚሰጡ የአእምሮ ጤና አገልግሎቶች ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ቢሰፉ፣ ለአእምሮ ጤና ህክምና የሚረዱ ስልጠናዎች ቢሰጡ የሚሉ ሀሳቦችን ያነሱት የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ናቸው ።

አሁናዊ የአእምሮ ጤና ያለበትን ደረጃ እና ቀጣይ የሚጠበቁ ተግባራትን የሚያሳይ ፓናል ውይይት፣ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ እና የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስነ አዕምሮ ጤና አገልግሎት መስጫ ጉብኝት ተደርጎ መድረኩ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *