
(ሆሳዕና፦ጥቅምት 14/2018)፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ስድስት የንቅናቄ ተቋማት አፈጻጸም የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራሮች በተገኙበት በዱራሜ ከተማ ተገምግሟል።የግምገማ መድረኩን የመሩት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ይሁን አሰፋና የጽህፈት ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ይግለጡ አብዛ ናቸው።
በመድረኩ ጤና፣ገቢ፣ንግድና ገበያ ልማት፣ግብርና፣ምግብ ዋስትና እና ስራ ዕድል ፈጠራ በተመለከተ የየተቋማቱ የስራ ሃላፊዎች በጥንካሬና በጉድለት የተለዩ ጉዳዮችን ሪፖርት አድርገዋል።በተለይም የወባ በሽታ ስርጭት እየተስፋፋ በመምጣቱ በሽታው የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በተመረጡ የክልሉ አካባቢዎች አመራሩ የተለየ ትኩረት በመስጠት የተጠናከረ የመከላከል ስራ እንዲሰራ ጥሪ ቀርቧል።
በገቢ አሰባሰቡ የሚታዩ ማነቆዎችን በቅንጅት መፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ጠንካራ ውይይት በማድረግ የመፍትሄ አቅጣጫዎች በመድረኩ ተቀምጠዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች መልካም ቢሆኑም ተጨማሪ መሬቶችን በማረስ ምርታማነትን ማሳደግና የተቀመጠውን ግብ ማሳካት እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።
በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ኢንሼቲቮችን በመቅረጽ ወደታች ለማውረድ የተደረጉ ጥረቶችና የተገኙ ስኬቶች በመድረኩ ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ሌሎች ስኬታማ የዘርፉ እንቅስቃሴዎችም ሪፖርት ቀርቧል።
በንግድና ገበያ ልማት ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችና ህገወጥነትን ለመከላከል እየተወሰዱ የሚገኙ ህጋዊ እርምጃዎችና አሰራሮች የቀረቡ ሲሆን፤ክልላዊ የስራ ዕድል ፈጠራ ጥንካሬዎች፣ጉድለቶችና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
በሁሉም የንቅናቄ ተቋማት የተጀመሩ አበረታች ስራዎችን አመራሩና ህዝቡ ይበልጥ ተቀራርበው በመስራት ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባና ማነቆዎቹንም በጋራ መፍታት እንደሚገባም የጋራ አቅጣጫ መቀመጡን ከፓርቲ ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።



