
በዛሬው እለት ከቻይናው የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ባለስልጣን (Chinese Disease Control and Prevention Authority /CDCPA/) የመጡ የልኡካን ቡድን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ሊሰሩባቸው በሚችሉ መስኮች ላይ መክረዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እንግዶቹን በተቀበሉበት ወቅት ከዚህ ቀደም በሁለቱ ሀገራት ግንኙነቶች የተደረጉ የሰው ሀይል አቅም ግንባታና ስልጠና እንዲሁም የልምድ ልውውጥ ተግባራት አመርቂ ውጤቶች ማስገኘታቸውን በመግለጽ በአሁኑ ወቅት ኢንስቲትዩቱም የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የጤና እና የስነ ምግብ ችግሮች ላይ ምርምር በማድረግ፣ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በመተንበይ፣ በመከታተልና በመቆጣጠር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ እና የላቦራቶሪ አቅምን በመገንባት እና የተለያዩ ደጀን የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ለልዑካኑ አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ በመቀጠልም ከነዚህ ተግባራት በተጨማሪም በተላላፊ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር፣ በድንበር ተሻጋሪ የህብረተሰብ ጤና ስጋቶች፣ በሰው ሃይል አቅም ግንባታ ዙሪያ ሁለቱ አገራት በጋራ በትብብር ለመስራት ኢንስቲትዩቱ ያለውን ዝግጁነት ተናግረዋል፡፡
የቻይናውን ልዑክ የመሩት ሚስተር ዥያንግ ሺ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አድንቀው ቻይናም ከበሽታ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም በአጠቃላይ የጤና ትምህርት ረገድ ልምድ ያዳበረች በመሆኑ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎትና ግንኙነታቸውንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡


