
በኢትዮጵያ የመቀንጨር ተጋላጭነትን ለመቀነስ የምግብ ሥርዓት ፍኖተ ካርታ በማስቀመጥ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ትግበራ ለወጣቶች፣ ለሕፃናት በተለይ ለታዳጊዎች ጉልህ ሚና አለው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን በማስተባበር እየተሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የሰቆጣ ቃልኪዳንን በማስቀመጥ ወደ ተግባር መግባቷን አንስተዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት መቀንጨርን ከመከላከል ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት በተሰራው ሥራ፤ ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ላይ ውጤት መታየቱን አስረድተዋል።
የመቀንጨርን ተጋላጭነት ለመቀነስ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የትምህርት ቤት ምገባዎች፣ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች እንዲሁም በግንዛቤ ፈጠራ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብን ከማረጋገጥ አንፃር ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በቅርቡ በተዘጋጀው የምግብ ሥርዓት ፍኖተ ካርታ አማካኝነት ከምርት ጀምሮ ለምግብነት እስኪቀርብ ድረስ ያለውን ሒደት ጥራት ላይ እንዲመሰረት በማድረግ የሚመለከታቸው አካላት በመናበብ እንዲሰሩበት መደረጉን አስታውቀዋል።
በሄለን ተስፋዬ

