Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በጤናው የምርምር ዘርፍ ኢትዮጵያን ከፍ ካደረጓት ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መሆኑ ተገለፀ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በወባና ትኩረት በሚሹ በሽታዎች፣ ተላላፊ እና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፣ በምግብና በስነ-ምግብ እንዲሁም በስርዓተ ጤና ዙሪያ የተሰሩ የአንድ አመት የስራ እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማና የተሰሩ የምርምር ውጤቶች ስርጭት አውደ ጥናት ሐምሌ 23 እና 24 /2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል::

የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ የተሰሩ የምርምር ስራዎችን ከታቀዱ ተግባራት አንፃር ውጤታማ ስራዎች እና የታዩ ክፍተቶችን በመለየት ውጤታማ ተግባራትን ለማስቀጠል ብሎም የምርምር ውጤቶችን ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ ለማድረግ፣ ለሚቀጥለው በጀት ዓመት 2018 ዓ.ም እቅድ እንደ ግብዓት በመጠቀም የተሻለ የስራ መደላድል ለመፍጠር ነዉ።

ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በአዉደ ጥናቱ ላይ እንደገለፁት ለጤናዉ ዘርፍ የጥናትና የምርምር ስራዎች ከምን ጊዜውም በላይ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን፣ ለዚህም የጤና ሚኒስቴር በርካታ የጥናትና ምርምር ሰራዎች ላይ ትኩረት አድርጐ እየሰራ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለፖሊሲ፣ ለፕሮግራምና ለስትራቴጂ ግብዓት የሆኑ በርከታ ጥናቶችን መስራቱን አብራርተዋል።

ዶ/ር ደረጄ አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ ለመቶ ዓመታት በጤናው ዘርፉ የኢትዮጵያን ሕብረተሰብ ሲያገለገል የቆየ መሆኑን ጠቁመው በጤናው የምርምር ዘርፉ ኢትዮጵያን ከፍ ካደረጓት ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መሆኑን ተናግረዋል::

ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ዓለማ አንፃር በርከታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን፣ በጥናትና ምርምር ፣ የሕብረተሰቡን ጤንነት ከአደጋ በመጠበቅ በኩል፣ የክልል ጤና ቢሮዎችን፣ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶችን አቅም በመገንባት፣ የጤና መረጃዎችን በማሰብሰብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ እና በአገር አቀፍ ደረጃ የላብራቶሪ አቅምን ከፍ በማድረጉ በኩል ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛውን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል ::

ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የተደረጉ የምርምር ስራዎችን እና ውጤታቸውን አስመልክቶ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን የጤናው ዘርፍ ከሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር እና ቅንጅት በመፍጠር የሕብረተሰቡን ጤና ሊያበለፅግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል::

በምርምሩ ዘርፍ ኢንስቲትዩቱ ለአንድ አመት የስራቸውን በርከታ ስራዎች ሪፖርት እና የተለያዩ የምርምር ውጤቶች በመድረኩ ቀርበው ሰፊ ግምገማ እየተደረገ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የኢንስቲትዩቱ የማኔጅመንት አባላትና የምርምር ባለሙያዎች ፣ የክልል ጤና ቢሮ እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና የምርምር ተቋማት እንዲሁም የአጋር ድርጅቶች ተወካዮች በአውደ ጥናቱ ላይ እየተሳተፉ ደገኛሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *