Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመታዊ ጉባኤውን በወራቤ ከተማ እያካሄደ ነው።

(ሆሳዕና፣ ሀምሌ 8/2017)፤ ኢንስቲትዩቱ በመድረኩ የ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የበጀት አመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ይገኛል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት አመት አምስት የጤና ልማት ግቦችን ለማሳካት በትኩረት መሠራቱን አንስተዋል።

ሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋንን ማፍጠን፣ የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታን ማሻሻል፣ ህብረተሰቡን ከድንገተኛ አደጋ መጠበቅ፣ የጤና ኤክስቴንሽን ስራን በወረዳዎች ማጠናከርና የጤና ስርዓት ምላሽ ሰጪነትን ማሻሻልን ታሳቢ ያደረጉ ግቦችን ለማሳካት ስለመሰራቱ ተናግረዋል።

በክልሉ የተከሰቱ ወረርሽኞች በህብረተሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ በቅንጅት በተሰሩ ስራዎች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አቶ ሳሙኤል ጠቁመዋል።

በክልሉ የላቦራቶሪ አገልግሎት እንዲኖር ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተሰሩ ስራዎች እንዲሁም ከህብረተሰቡ ሀብት በማሰባሰብ ረገድ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን የቢሮ ኃላፊው አመላክተዋል።

ከወረርሽኝ ክስተቶች፣ ከሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን አንፃር የገጠሙና ሊገጥሙ የሚችሉትን ችግሮችን ለመፍታት በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል የተደራጀ የመረጃ ስርዓትን በበጀትና በግበዓት መደገፍ ይገባልም ብለዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው፣ የላቦራቶሪ አገልግሎት ደረጃ ማሻሻል፣ ማሳደግና ማስፋፋት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተጠቁሟል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ተለዋዋጭ የዓለም የጤና ስርዓቱ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ እያለፈ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በተለያየ ጊዜ የወረርሽኝ አሳሳና ቅኝት በማድረግ ለድንገተኛ ጤና አደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት አደጋዎች ሳይከሰቱ መከላከልና ቢከሰቱም ፈጥኖ መቆጣጠር ስለመቻሉ ተናግረዋል።

በመድረኩ ባለድርሻ አካላት፣ በክልሉ የሚገኙ ዩንቨርስቲ ተወካዮች፣ የዞንና ልዩ ወረዳ የጤና መዋቅር ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

በመላኩ አድማሱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *