Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በጤናው ዘርፍ መሻሻል እንዲመጣ የጥናትና ምርም ስራዎች ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2017 ዕቅድ አፈጻጸም ማጠቃለያ እና የ2018 ቀጣይ አቅጣጫዎች መድረክ በወራቤ ከተማ ተካሂዷል።

ሐምሌ 8/2017 ሀላባ ቲቪ

—————————-

በመድረኩ ላይ ለዕለቱ የተዘጋጀ ሰነድና የአፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምላሽና ማብራሪያውን የሰጡት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙዔል ዳርጌ በክልሉ የወባና ኮሌራ ወረርሽኝን የመቆጣጠር ልምድ እየዳበረ መምጣቱን አስታውሰው በቀጣይ በክትትል ማነስ ክፍተት እንዳይፈጠርና ወረርሽኙ ችግር በማይሆንበት ደረጃ ማድረስ አለብን ብለዋል።

በምግብና ስርዓተ-ምግብ ዘርፍ በክልላችን የልማት ትራፋት እና የ30፣40፣30 ዘርፍ እንዲሁም ከተረጅነት ወደምርታማነት ሽግግር ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራና የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ እህል የማከማቸት ስራ እንደተሰራ ተናግረዋል።

አክለውም ኢንስቲትዩቱ ስራዎችን ከአምናው በተሻለ አፈጻጸም እንዳከናወነ ገልፀው የጤና ስራዎቹ ከግብ እንዲደርሱ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በትብብር ሲሰሩ የነበሩ ዩንቨርስቲዎችን፣ ኮሌጆችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ዘርፍ ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አስረድተዋል።

ከዩንቨርስቲዎች ጋር በመተባበር በጥናትና ምርምር ዘርፍ በዚህ ዓመት ከፍተኛ የጥናትና ምርምር ስራዎች መሰራቱን እና የጥናቱ ውጤትም ተግባራዊ መደረጉን አብራርተዋል።

የሴቶች ልማት ህብረት ጉልህ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ይህ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጴጥሮስ በበኩላቸው ከላብራቶሪ አንፃር ትልቁ የሪፎርም ስራ እንደመሆኑ መጠን አሁን ያለውን ሽፋን ከፍ ለማድረግ መስራት አለብን ብለዋል።

አያይዘውም የደንበኞች እርካታን ለማሳደግ የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግ ይገባናል ብለዋል።

ከጥናትና ምርምር ስራዎች አንፃርም የምርምር ሥራውን ከነበረበት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ ሃጂ መሐመድናስር፣ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር የማሕበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሳሙኤል ገብረ-ሚካኤል፣ የክልሉ ጤና ቢሮ የዘርፍ ኃላፊዎችና ማኔጅመንት አባላት፣ የዩንቨርስቲ ተወካዮች፣ እንዲሁም ከዞንና ልዩ ወረዳ የጤና ሴክተር ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በመሐመድ ሞክሼ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *