
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በምስራቅ ጉራጌ ዞን በህብረተሰብ ተሳትፎና በክልሉ መንግስት ገንዘብ ወጪ የተገነባውን የንቡር ሁሉ አቀፍ ጤና ኬላ ስራ አስጀመረ።
ለሁሉ አቀፍ ጤና ኬላ ግንባታው የአካባቢው ህዝብና የክልሉ መንግስት ከ13ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸው ተገልጿል።
የጤና ተቋሙን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የብልጽግና መንግስት የህብረተሰቡን የጤና ሽፋን ለማሳደግና የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት 17 ሁሉ አቀፍ ጤና ኬላዎችን በመንግስትና በህዝብ ድጋፍ ለማሰራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልጸው ፣ህብረተሰቡ ለአዳዲሶቹ ተቋማት የጎደሉ ቁሳቁሶችን ለማሟላት እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል።
የአካባቢው ህዝብ የተገኘውን ሰላም በመጠበቅና በማጽናት ልማቱን እንዲያፋጥንም አቶ ሳሙኤል አሳስበው ፣የጤና ተቋሙ በአጎራባች የሚገኙ ህዝቦችን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን የሚያጎለብት ትልቅ ተቋም መሆኑንም አስታውቀዋል።
ሁሉ አቀፍ ጤና ኬላው ለምስራቅ መስቃን ወረዳ፣ለአጎራባች የማረቆ ልዩ ወረዳ ቀበሌያትና ለኦሮሚያ ክልል አጎራባች ቀበሌያት ህዝቦች የተሻለ የጤና አገልግሎት እንደሚሰጥም አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል።
ንቡር ሁሉ አቀፍ ጤና ኬላ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን ወረዳ ወጃ ቀበሌ ይገኛል።
ለጤና ተቋሙ ግንባታ የአካባቢው ህዝብ ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብ፣በጉልበትና በሀሳብ ወጪ ያደረገ ሲሆን የክልሉ መንግስትም ለተቋሙ ግንባታ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል።
ሁሉ አቀፍ ጤና ኬላው የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢንሼቲቭ የሆነው የአንድ ወረዳ አንድ ፕሮጀክት አካል መሆኑም ተመላክቷል።
ከፍተኛ አመራሮቹ ከጤና ተቋም ምረቃው በኋላ የምስራቅ መስቃን ወረዳን የልማት ስራዎች የሚያሳይ አውደ ርዕይ በመመረቅ የአረንጓዴ አሻራቸውን በሁሉ አቀፍ ጤና ኬላው ግቢ ውስጥ አኑረዋል።
ሁሉ አቀፍ ጤና ኬላውን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ፣የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን፣የማረቆ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አማሮ፣የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ ጫካ፣፣ከፍተኛ የክልሉ ጤና ቢሮ የስራ ሃላፊዎች፣የዞኑና የወረዳው አመራሮች ናቸው።


