
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ጋር የእናቶችና ህጻናት ሞት እና የሞት መንስኤዎች እንዲሁም አጠቃላይ የበሽታ ሰርጭት የመለየት እና ያሉትን የክትትል ስርዓቶችን ለማጠናከር የናሙና ምዝገባ ስርዓትን (Sample Registration System/SRS/) ለመዘርጋት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የተፈረመ ሲሆን የማስጀመሪያ የዉይይት መድረክም ሰኔ 24/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት በኢትዮጵያ የወሊድ ሁኔታ የእናቶችና ህጻናት ሞት እና የሞት መንስኤዎችን ለመለየት የናሙና ምዝገባ ስርዓትን መዘርጋት ዘላቂ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የጤና ውሳኔ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን አመላክተው፤ እየተካሄደ የሚገኘው የናሙና ምዝገባ ሥርዓት የማስጀመሪያ ፕሮግራም እና የመግባቢያ ሰነድ በቀጣይ በቅንጅት መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በመተንተን፣ መረጃዎችን ተደራሽ በማደረግ እና በማጋራት፣ የተሻሉ የጤና ግንባታ ስራዎች የሚመዘገቡበት በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ በቅንጅት መስራታቸው እጅግ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራ ትንተና ማዕከል ያከናወናቸው ተግባራትን አስመልክቶ እንዲሁም የተለያዩ ጥናቶች በመድረኩ ቀርበዉ ዉይይት የተደረገባቸዉ ከመሆኑም በተጨማሪ የናሙና ምዝገባ ስርዓት (SRS) በመዘርጋት የመረጃ ክፍተቶች እንዳይኖሩ በማድረግ በሀገሪቷ ያለውን የጤና ልማት እና ኢንቨስትመንት እቅድ ለማሳካት እንዲሁም በማስረጃ የተደገፉ ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚረዳ ፕሮግራም መሆኑ በመድረኩ የቀረበ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የኢንስቲትዩቱ የማኔጅመንት አባላት፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች፣ የአፍሪካ ሲዲሲ፣ ጆንሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሌሎች አጋር ድርጅቶች በዝግጅቱ ላይ ታድመዋል።


