
የማእከላዊ ኢትዩጲያ ክልል ጤና ቢሮ እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የተቀናጀ የኩፍኝ እና ፖሊዮ ክትባት፤ ስርአተ ምግብ፤ እናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎት ዘመቻ እንዲሳካ ላደረጉት ጥረት እውቅና ተሰጣቸው !
___________
በኢትዮጵያ የተቀናጀ የኩፍኝና የፖሊዮ ክትባት፣ሥነ-ምግብ እና የእናቶችና ሕጻናት ጤና አገልግሎት ዘመቻዎች ስኬታማ መሆናቸውን ለመገምገምና እውቅና ለመስጠት ልዩ ስብሰባ ተካሂዷል። ዝግጅቱ ያተኮረው በግንቦት ወር በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የተቀናጀ የክትባት ዘመቻ ውጤታማነት ስኬቶችን መገምገም እና በዘመቻው አስተዋጾ ላበረከቱ አካላት እውቅና ለመስጠት ነው።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ ቁልፍ ግቦች የሆኑትን የእናቶችና ህጻናትን ሞት በመቀነስ ጤናን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል። ዘመቻው በተሳካ ሁኔታ ሀብትና የሰው ተሰጥኦ በመጠቀም በርካታ የጤና አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ በአንድ ጊዜ ለማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል። ዶ/ር መቅደስ ለዘመቻው ስኬት አስተዋጾ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ዘመቻው በፌደራል፡ ክልሎችና ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የተሰራ እና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የላቀ ስኬት የተገኘበት መሆኑን ጠቁመው፤ ከ18.5 ሚሊዮን በላይ ህጻናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ተሰጥቷቸዋል፣ ከነዚህም መካከል ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከዚህ በፊት ክትባት ወስደው የማያውቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እንደተናገሩት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በተደረገ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ22 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከ5 አመት በታች ለሆኑ ህጻናት ክትባቱ መድረሱን ተናግረዋል። ከጎረቤት ሀገራት ኬንያ እና ሶማሊያ ጋር በመተባበር ከ10,000 በላይ ህፃናት በመግቢያ እና መውጫ ኬላዎች እንዲከተቡ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶ/ር ኦወንስ ካሉዋ የክትባት ዘመቻው በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ በመሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናትን ህይወት መታደጉን በመጥቀስ የጤና ሚኒስቴርን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። በተመሳሳይ የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ማሪኮ ካጉሺማ የዘመቻው ስኬት የቅንጅት እና የአመራር ሃይልን ያሳየ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
በተቀናጀ የክትባት ዘመቻው የኩፍኝ እና የፖሊዮ ክትባት የተሰጠ ሲሆን፤ የስርአተ-ምግብ ችግር ያለባቸው ህጻናት ልየታ፣ የታመሙ ህጻናት እና እናቶች ልየታ መካሄድ መቻሉ ታውቋል፡፡ በመድረኩ በተቀናጀ የክትባት ዘመቻው አስተዋጾ ላበረከቱ የክልል የጤና ቢሮዎች፣ የክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና የልማት አጋር ድርጅቶች እውቅና ተሰጥቷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በክልላችን ይህ ተግባር አንዲሳካ የተሳተፋቹ ባለድርሻ አካላትን በክልሉ ስም እናመሰግናለን ።