
ፈጠራን ባሕል በማድረግ የሕክምና ዘርፉን መደገፍ ይገባል ሲሉ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽን እና ጥራት ጉባኤ ዛሬ 2ኛ ቀኑን ይዟል።
በጉባኤው ላይ “ፈጠራ ሁሌም ጥራትን ለማምጣት ይረዳል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ፈጠራ የታከለበት ስራ የጤና ዘርፉን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ የጤና ተደራሽነትና ጥራት ላይ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተው፤ ጥራት ያለው ስራ ለማከናወን እንዲረዳም የዘርፉን የአመራር አቅም ለመገንባት በርካታ ስራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል።
የጤናው ዘርፍ የቁጥጥር ስራዎች በማሳደሰግ ከ18 በላይ የጤና የጥራት መለኪያዎችን መውጣታቸውን ጠቁመው፤ በተጨማሪ ጥራትን ለማሳደግ የጤና ግብዓት አቅርቦትን የሚያሻሽሉ አዋጆችን ለመከለስ ጥረት መደረጉንም ነው የገለጹት።
ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች የጤና መድህንን ከ63 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የጤናው ዘርፍ ሰፊ በጀት እንደሚፈልግ አንስተው፤ ስራዎችን በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የጤናው ዘርፉ ላይ እክል እየፈጠሩ የሚገኙ የቅንጅት ውስንነቶችንና የዲጂታላይዜሽን አጠቃቀም ክፍተትን ማሻሻል እንደሚገባም ነው የገለጹት።
በሜሮን ንብረት
