Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የዓለም ቆልማማ እግር ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ተከበረ ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴርና Hope Walks ጋር በመተባበር የዓለም ቆልማማ እግር ቀንን በቡታጅራ በግራር ቤት የተሃድሶ ማዕከል ከታካሚ ህፃናትና ቤተሰቦቻቸው ጋር ተከበረ ::

የዘንድሮ የአለም የቆልማማ እግር ቀን ” ወቅታዊ ፣ ውጤታማ ፣ ተደራሽ የዞረ እግር ህክምና ለሁሉም ህፃናት ” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመሳሳይ ቀንና ጊዜ በሀዋሳ ከተማ የተከበረ ሲሆን በክልላችን ለሁለተኛ ጊዜ ከሚደረገው አከባበር ጋር በ2ኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ዘመቻ ወቅት ለተለዪ የቆልማማ እግር (Club Foot) ነፃ ህክምናና ክትትል ማስጀመሪያ ፕሮግራምም ማቀናጀት ተችሏል።

በየአመቱ ግንቦት 26 የሚከበረው የቆልማማ እግር ቀን ከአፈጣጠር ችግሩ ጋር ተወልደዉ በህክምናና ክትትል ከችግሩ የተላቀቁትን፣ ከዘላቂ የአካል ጉዳተኝነት የተረፉትን እንዲሁም በቀጣይ ችግሩ ቢከሰት በቀላሉ መታከም መቻሉ እንዲሁም በክልላችን እንደ አዲስ የተጀመሩ የቆልማማ እግር ነፃ የህክምና ማዕከላት እድሎችን በማሰብ በደስታ የሚከበር ቀን ነዉ።

ፕሮግራሙን የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ጤና ቢሮ ህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ዳዊት ዳንኤል፣ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ ፣ የስልጤ ዞን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ ሀይረዲን፣ የወራቤ ኮ/ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ካሊድ ሸረፋ እና የቡታጅራ ግራር ቤት የተሃድሶ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ቱሉ በይፋ አሰጀምረዋል።

በዝግጅቱ በተፈጥሮ የዞረ እግር ህክምና መስጫ እና ማስተማሪያ ማዕከል እንዲሁም የታካሚ ህፃናት መካነ መጫወቻ (Renovated ClubFoot Treatment, Training Center and Play corner) ተጎብኝቷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል በይፋ ሥራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ከ450 በላይ ህፃናት ነፃ የቆልማማ እግር ህክምናና ክትትል በመደበኛና የዘመቻ ፕሮግራሞች የታከሙ ሲሆን የቆልማማ እግር ህክምና መስጫ ማዕከላትንም ( Club Foot Clinics) ከ3 ወደ 6 በእጥፍ ማሳደግ ተችሏል።

ቀደም ሲል በቡታጅራ ግራር ቤት የተሃድሶ ማዕከል፣ በንግስት ኢሌኒና የወራቤ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ብቻ ሲሰጥ የነበረ አገልግሎት በአሁን ጊዜ የሀላባ አጠቃላይ ሆስፒታል ፣ የዱራሜ ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታልና የወልቂጤ ዪኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የቆልማማ እግር ህክምና እንደ አዲስ የጀመሩ ማዕከላት ናቸው።

ከ30 ዓመት በፊት ግራር ቤት የተሀድሶ ማዕከል በሚል ስራ የጀመረው ይህ ሆስፒታል ለበርካታ ወገኖች ተመጣጣኝ የጤና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ይህ በቀላሉ ሊታከም የሚችል ችግር በጊዜዉ ባለመታከሙ ምክንያት በርካቶችን የእድሜ ልክ የአካል ጉዳተኛ ያደርጋቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *