
ግንቦት 22/2017 ዓ.ም
በማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የምስራቅ ጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ በሁለተኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከግንቦት 22-25/2017 ዓ.ም ድረስ ለ4 ቀናት ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሁለተኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ መከላከያ ዘመቻ እንደዞን ከ93 ሺ 117 በላይ ህጻናት ለመከተብ ዕቅድ መያዙን ገልፀዋል።
በዘመቻው ከፖሊዮ መከላከያ ክትባት ባሻገር ተጓዳኝ የጤና ተግባር የሆኑት እንደ የቆልማማ እግር፣ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ህጻናት፣ የማህጸን ወደ ውጭ የመውጣትና ፌስቱላ ችግር ያለባቸው እናቶች ልየታ የሚደረግ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ ዞን ክትባቱ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመስጠት አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ የተሰራ እንደሆነ እና ሁሉም ህፃናት የክትባቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሪሰርች ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ስናፍቅሽ አየለ በበኩላቸው የክትባት ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆን የአመራሩ ሚና ትልቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
ፖሊዮ በሽታ ህፃናትን ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ እንደሆነ ነገር ግን ከመከሰቱ በፊት በክትባት መከላከል የምንችለው በሽታ እንደሆነ ተናግረዋል።
የፖሊዮ ክትባት ውድ እና በእርዳታ የሚገኝ ስለሆነ ለህፃናቱ ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም አካል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የእንሴኖ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሸይቾ ኢብራሂም በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ተወካይ ዶ/ር ፋንታሁን ይማም ፣የእንሴኖ ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ሸምሱ አደም ጨምሮ የዞኑ ጤና መምሪያ የማኔጅመንት አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።



