
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የላቦራቶሪ ውጫዊ ጥራት ቁጥጥር መረጃ አያያዝ ስርዓት መበልፀጉ፣ ለፕሮግራሙ ስኬት ትልቅ ምዕራፍ መሆኑ ተገለፀ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ፣ የላቦራቶሪ ውጫዊ ጥራት ቁጥጥር ተግባራት መረጃ አያያዝ ስርዓትን ለማጠናከር ታቅዶ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበለፀገና “NATIONAL ET-EQAS” የተሰኘውን Software Database ስልጠና በአገር አቀፍ ደረጃ የአሰልጣኞች ሥልጠና ከተሰጠ በኋላ፣ በክልሉ ለሚገኙ የውጫዊ ጥራት ቁጥጥር ማዕከላት ባለሙያዎች እና የወረደ ኦፊሰሮች በሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
የ “NATIONAL ET-EQAS” ሶፍትዌር ዳታቤዝ፣ ሁሉንም የጥራት ቁጥጥር ተግባራትን፣ ማለትም የወባ እና ቲቢ ስላይድ መልሶ ምልከታ (Random Blinded Rechecking)፣ የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን ብቃት መመዘኛዎችን (Proficiency Testing)፣ የድጋፋዊ ክትትል እና ሌሎች ተግባራት፣ ከወረቀት ነፃና ኦንላይን ስርዓት መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የማደራጀት፣ የመተንተን እና ግብረ መልሶችን ለጤና ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በቀላሉ መስጠት የሚያስችል መሆኑ ተገልፀጿል።
የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ አቶ ግርማ ወንድሙ ለሰልጣኞች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የ“NATIONAL ET-EQAS” ሶፍትዌር ዳታቤዝ መበልፀጉ፣ ለውጫዊ ጥራት ቁጥጥር ፕሮግራም ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን እና በሀቀኛ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ሰጪነትን እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።
የክልሉ ላቦራቶሪ ዳይሬክተር እንደገለፁት ከሆነ፣ “ይህ ሶፍትዌር የEQA Program ተግባራትን ከማቅለል ባለፈ፣ ከዚህ በፊት በፕሮግራሙ ዙርያ የሚታዩ ችግሮችን የምንሻገርበት እና ከጠቀሜታው አንፃር ማንኛውም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የሰልጣኞች ቁርጠኝነት ያስፈልጋል” ብለዋል።
በተጨማሪም የክልሉ መንግስት ጤና ቢሮ፣ በሁሉም የጤና ዘርፍ ክልሉ በአገር ደረጃ ከፍተኛ አፈፃፀም እንዲመዘግብ እና ፊት የወጣ ክልል እንዲሆን የክልሉ መንግስት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ጠንካራ እና የተቀናጀ የላቦራቶሪ ውጫዊ ጥራት ቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት እና ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት ለተገልጋይ ማህበረሰቡ እንዲደርስ፣ ሁሉም የላቦራቶሪ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የ“NATIONAL ET-EQAS” ሶፍትዌር ዳታቤዝ ስልጠና፣ ከ12ቱም የውጫዊ ጥራት ቁጥጥር ማዕከላት ሆስፒታሎች ለተውጣጡ 25 የላቦራቶሪ ሃላፊዎችና የጥራት ቁጥጥር ኦፊሰሮች፣ እንዲሁም ለ70 የቲቢ እና ወባ ስላይዶችን ለሚሰበስቡ የወረዳ/ከተማ አስተዳደር ፎካሎች በሶስት ዙር የሚሰጥ ሲሆን፣ የሰለጠኑት ባለሙያዎች ያገኙትን እውቀትና ልምድ አብረዋቸው ለሚሰሩ ሌሎች ባለሙያዎች የማካፈል ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

