Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ በይፋ ስራ ጀመረ::

በወራቤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቅጥር ጊቢ የሚገኘው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ ዛሬ ሚያዝያ 29/2017 በይፋ ስራ ጀመረ።

ዶ/ር ሳሮ አብደላ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክትር በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ላቦራቶሪው ለክልሉ ሕብረተሰብ ጥራት ያለውና የላቀ የጤና ምርመራ አገልግሎት መስጠት የሚችል እና ከ30 በላይ የበሽታ አይነቶችን መመርመር የሚያስችል ማሽኖች በላቦራቶሪው እንደሚገኙ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ጠቅሰው፣ የጨቅላ ህፃናት የኤች አይ ቪ፣ የጉበትና መሰል በሽታዎችን በጥራት መመርመር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክትርን መልዕክት ያስተላለፉት የኢንስቲትዮቱ ዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር አማር ባርባ እንደገለፁት በዓለማችን ላይ በተለያዩ ለውጦች ምክኒያት የህብረተሰብ ጤና ስጋቶች እየጨመሩ ይገኛሉ፡- ተላላፊና ዳግም እየተከሰቱ የሚገኙ በሽታዎች፣ የፀረ-መድሃኒት ብግርነት መጨመር፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች መበራከትና እየከፋ መምጣት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ቀድሞ መተንበይ፣ መከላከል፣ መቆጣጠርና ምላሽ መስጠት እንደ አመራር ከኛ የሚጠበቅ ግዴታ ስለሆነ ይህ ላብራቶሪ ይህንን ኃላፊነታችንን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችለን መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የጤናው ዘርፍ ልማት ኢንቨስትመንት ዕቅድን ለማሳካት የሕብረተሰብ ጤና ላቦራቶሪ ማቋቋም፣ በቴክኖሎጂ በማዘመን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባ እስረድተዋል።

የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው በክልሉ ከዚህ ቀደም የህብረተሰብ ጤና ላብራቶሪ ባለመኖሩ፣ የምርመራ አገልግሎት ከሌላ ስፍራ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው ክልላዊ ላቦራቶሪ መቋቋሙ ይህን መሰል ችግሮችን በመቅረፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አብራርተው፣ በክልሉ ለተቋቋመው የህብረተሰብ ጤና ላቦራቶሪ እውን መሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ከላቦራቶሪው ይፋ ማስጀመሪያ ስነ ስርዐት በፊት ዶ/ር ሳሮ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከክልሉ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የተለያዩ ሆስፒታሎችንና የጤና ተቋማትን ጎብኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *