Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ለድንገተኛ የጤና ቀውስ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ለድንገተኛ ወረርሽኝ እና የጤና ቀውስ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የሩሲያ የዜጎች ጤና እና የሸማቾች መብት ጥበቃ አገልግሎት ኃላፊ ዩ ፖፖቫ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ለፈጣን ምላሽ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከማቅረብ ባለፈ የዘርፉ ባለሙያዎችን ብቁ የሚያደርግ ስልጠናን ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡

ይህም ለዘርፉ ከሚያበረክተው እገዛ ባሻገር የእውቀት ሽግግርን የሚያሳልጥ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገልፀዋል፡፡

በዚህም በሽታ መከላከል፣ ቀድሞ መመርመር እና ፈጣን ምላሽ መስጠት ላይ ያለ አቅምን ማጠናከር እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

ዶክተር መቅደስ እደገለጹት፤ ለሚከሰቱ የጤና ቀውሶች ተገልጋዩ ወደ ላብራቶሪው መሄድ ብቻ ሳይሆን ላብራቶሪው ወደ ማህበረሰቡ በመሄድ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ የሚያስችል ‘የሞባይል ላብራቶሪ’ በሩሲያ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

“ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ያስገኘላት ዕድል ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፤ አጋርነቱ የረጅም ዓመታት ትስስር ያለውን የሁለቱን ሀገራት መስተጋብር ያጠናከረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የሩሲያ የዜጎች ጤና እና የሸማቾች መብት ጥበቃ አገልግሎት ኃላፊ ዩ ፖፖቫ በበኩላቸው፤ መርሐ ግብሩ ከተረጂነት በማላቀቅ ዘላቂ እገዛን ያነገበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ኢትዮጵያ እና የትኛውንም የአፍሪካ ሀገር በቅኝ ያልገዛችው ሩሲያ እልፍ የሚያቆራኛቸው ጉዳዮች አሉ ሲሉ ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡

ወረርሽኝ እና የጤና ቀውስ ድንበር የለሽ ክስተት በመሆኑ ይህ እገዛ እና ስልጠና ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው የጤና ባለሙያዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚበቃ መሆኑን አያይዘው አመላክተዋል፡፡

በአፎሚያ ክበበው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *