Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በ7ኛው ዙር የጤና አመራርነት ኢንኩቤሽን ፕሮግራም 57 ሰልጣኞች ተመረቁ

ስልጠናውን ላጠናቀቁ ሰልጣኞች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከእርዳታ ተላቀን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ ለመድረስ ቁርጠኛ የሆነ አመራርን አስፈላጊነት አጽኖት ሰጥተዋል፡፡ በጤናው ዘርፍም ቢሆን ነገን ለመቀየር ብቃት ያለው አመራር ለመፍጠር የፕሮግራሙን አስፈላጊነት ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሙ በተለይ ለሴቶች ትኩረት በመስጠት በዚህኛው ዙር አብላጫውን ድርሻ እንዲይዙ መደረጉን የተናገሩት ዶ/ር መቅደስ፤ ተመራቂዎች ግንባር ቀደም በመሆን የሚያጋጥሟቸውን እድሎች ሁሉ ተጠቅመው መቀየር የሚችሉትን ሁሉ በተግባር እንዲቀየሩ መክረዋል፡፡ ተመራቂዎች በሚሄዱበት ሁሉ የጤና አምባሳደር በመሆን እለት ተእለት እውቀታቸውን ማዳበር እንዳለባቸውም አክለው ተናግዋል፡፡

ሰልጣኞቹ የቀሰሙትን እውቀት ተቋማቸውን፣ ማህበረሰባቸውን እና ሃገራቸውን በብቃት እንዲያገለገሉ ይረዳቸዋል ያሉት ደግሞ የአሜሪካን ኢንተርናሽናል ሄልዝ አሊያንስ የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳሬክተር ቅድስት ሃይሉ ሲሆኑ፤ መሪነት ማቀድ ብቻ ሳይሆን መተግበርንም ይጨምራል፤ ተመራቂዎች እውቀታቸውን በመጠቀም ሌሎችን በማብቃት ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው ተናግዋል፡፡

ፕሮግራሙ የተቀረጸው በጤና ዘርፍ ቁርጠኝነት እና የላቀ ክህሎት ያላቸውን ግለሰቦች በመመልመል ለአመራርነት ለማብቃት መሆኑን ያስረዱት በጤና ሚኒስቴር የጤና ኢኖቬሽን እና ማሻሻያ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አባስ ሃሰን ሲሆኑ፤ ሰልጣኞች የጤናው ዘርፍን በመምራት በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን፤ የእውቅና መርሀ-ግብር እና የፓናል ውይይትም ተካሂዷል፡፡

የጤና አመራር ኢንኩቤሽን መርሃ ግብር ለተመራቂዎች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ሰፊ የጤና ስርዓትም ጠቃሚ ነው። ቁርጠኛ እና እውቀት ያላቸው መሪዎችን በማብቃት፣ መርሃግብሩ ይበልጥ የመቋቋም አቅም እና ውጤታማ የጤና እንክብካቤ ማዕቀፍን ለማጎልበት አስተዋፅኦ ያደርጋል፣ ይህም የተሻለ የጤና ውጤቶችን ያስገኛል።

መረጃው ጤና ሚኒስትር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *