
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሳምንታዊ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ EOC ግምገማ አካሂዷል
የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ በሳምንቱ ዉስጥ የተከናወኑ ቅኝትና ምላሽ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ዉይይት ተደርጎባቸዋል ።
የቢሮው ጤናና ጤና ነክ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘሪሁን ደሞዜ የሳምንቱን ሪፖርት ሲያቀርቡ ባለፈው ሳምንት 4801 የወባ በሽታ መከሰቱን ጠቁመዉ በዚህ ሳምንት 5461 ሰዎች በወባ በሽታ የተያዙ ሲሆኑ ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር 13.8 በመቶ መጨመሩን በሪፖርታቸው ገልጸዋል ።
በዚህ ሳምንት በወባ በሽታ የሞት ሰዉ የለም ያሉት አቶ ዘሪሁን በሳምንቱ 27 የወባ ታማሚዎች በተለያዩ ተቋማት ተኝተው እየታከሙ ስለመሆናቸዉ አመላክተዋል ።
በክልሉ በዚህ ሳምንት ዉስጥ ጠምባሮ ልዩ ወረዳ፣ ሽንሽቾ ከተማ አስተዳደርና ማረቆ ልዩ ወረዳ ከፍተኛ የወባ ጫና የተከሰተባቸዉ አካባቢዎች መሆናቸዉ ከመድረኩ የተገለፀ ሲሆን ልዩ ትኩረት እንደሚያሻቸዉ ተመላክቷል
አቶ ዘሪሁን አክለዉም በሳምንቱ ዉስጥ 16 የጨቅላ ህፃናት ሞት ሪፖርት መደረጉንም አንስተዋል
በክልሉ 409 ህፃናት በምግብ እጥረት የተጎዱ መሆናቸዉን የጠቆሙት ባለሙያ ከነዚህም ዉስጥ 69 በመቶ በተኝቶ ህክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ከባለፈዉ ሳምንት ጋር ሲነፃፀር 15.7 በመቶ መቀነስ መቻሉን ጠቁመዋል
የጤና ኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጴጥሮስ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በክልል ደረጃ የወባ ጫና በሚፈለገዉ ልክ እንዲቀንስ እና በቀጣይ ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል የንቅናቄው ስራ እና ግንዛቤ የመፍጠር ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
ከወባ በሽታ ነፃ የሆኑ አካባቢዎችን ለመፍጠር የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እና የየግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በማጠናከር ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ለገሰ በባለፉት ጊዝያት የወባ ጫና የቀነሰባቸዉን ተሞክሮዎች በመለየት በቀጣይ ዉጤት ሊያመጣ በሚችል መልኩ በልዩ ተኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል
እንደ አቶ ለገሰ ገለፃ ከየመዋቅሩ የሚላኩ የክትባትና የሌሎች ተግባራት ሪፓርቶች ወጥ እና ትክክለኛ እንዲሁም የተደራጀ እና ተአማኒነት ያለዉን መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አክለዋል
በመድረኩም በክልሉ በወባ ወረርሽኝ እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በሳምንቱ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ዉይይት ተደርጎባቸዉ ዉይይቱ ተጠናቋል ፡፡
በሸምሲያ አደም


