
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣዉን ኤችአይቪ ኤድስና ቫይራል ሂፓታይተስን ለመከለል እና ለመቆጣጠር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የዘርፈ ብዙ ኤች አይቪ ኤድስ መከ/መቆ/ዳይሬክቶሬት ለቢሮዉ ሰራተኞች በወቅታዊ የኤችአይቪና ቫይራል ሄፓታይተስ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በወራቤ ኮምፕሬሄንሲቪ ሆስፒታል ዉይይት አድርገዋል ፡፡
አቶ አለማየሁ ጌታቸው በጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ እና ዘርፈ ብዙ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መድረኩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣዉን ኤችአይቪ ኤድስና ቫይራል ሂፓታይተስን ለመከለል እና ለመቆጣጠር የቢሮዉን ሰራተኛ ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በተያዘዉ በጀት ዓመት በክልል ደረጃ 8650 የህብሰተሰብ ክፍሎች ባደረጉት የደም ልገሳ ዉስጥ 560 ዜጎች የተበከለ እና ለአገልግሎት የማይውል ደም መለገሳቸዉን የጠቆሙት አቶ አለማየሁ ከነዚህም ዉስጥ ቫይራል ሂፓታይተስ ዋኘኛዉና ቀዳሚዉ መሆኑን ተናገረዋል።
ቫይራል ሂፓታይተስ የገዳይነት ምጣኔዉ ከኤች አይቪ ሻይረስ በላይ ስለመሆኑ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የቢሮው ሰራተኞች በኤችአይቪ እና ቫይራል ሄፓታይተስ ዙሪያ ያላቸውን ወቅታዊ መረጃ በየጊዜው በማሳደግ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸዉን ከበሽታዉ መታደግ ይገባል ብለዋል።
አቶ ሀብታሙ ሀይለ መስቀል የዘርፈ ብዙ ኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዉስጥ የሲዲሲ ፕሮጀክት አስተባባሪ የዉይይት ሰነዱን ባቀረቡበት ወቅት ላይ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ግመታ መሠረት በክልላችን 15,276 ወገኖች ኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው እንደሚገኝ ጠቅሰው 438 የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በየአመቱ አዲስ በኤች አይቪ እንደሚያዙና 270 ሰዎች ደግሞ እንደሚሞቱ በሪፖርታቸዉ አመላክተዋል።
አቶ ሀብታሙ አክለዉም ኤች አይቪን ጨምሮ ሌሎች አጋላጭ ከሆኑ ተግባራት በመቆጠብ የራሳችንና የቤተሰቦቻችንን ጤንነት የመጠበቅ ሀላፊነታችንን መወጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
የዉይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ይህ ስልጠና ለመንግሥት ሰራተኞች የማንቅያ ደወል መሆኑና ራሳቸውን ከኤች አይቪና ከቫይራል ሂፓታይተስ እንዴት መከላከል እንደሚችሉ መሰረታዊ እዉቀት ያገኙበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰው ስልጠናዉ ቀጣይነት ሊኖረዉ እንደሚገባ አንስተዋል
በመድረኩ የቢሮዉ የማነጅመንት አካላት እና የቢሮዉ ሰራተኞች ተሳትፈዋል ።
በሸምሲያ አደም


