
በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ የተመራ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና ከኢትዮጵያ መድሀኒት አቅርቦት አገልግሎት የተውጣጣ የከፍተኛ አመራሮች ቡድን በሀገራችን መድሃኒት እያመረቱ ከሚያቀርቡ የፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪዎች አንዱ የሆነውን ሂውማንዌል ፋርማሲዩቲካል ኢትዮጵያን ጎብኝቷል።
የሀገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪዎች በአቅርቦት ያላቸው ድርሻ እየጨመረ መሆኑን የጠቆሙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ የሀገር ውስጥ የመድሀኒት አቅርቦት ማደጉ ዘለቄታ ያለው የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል ወሳኝ እንደመሆኑ መጠን ምርቶቹ በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ ደረጃ በጥራት ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቀደም ሲል የሀገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት ያጋጥም የነበረው ችግር ደረጃ በደረጃ መፈታቱን የጠቆሙት ወ/ሮ ፍሬሕይወት ጤና ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል። ለዚህም ስኬት የሀገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ፎረም በማቋቋም ወደ ስራ መገባቱን ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ በበኩላቸው ከግንባታ ዲዛይን ጀምሮ ተቋማቸው ድጋፍ በማድረግና ግብረ መልስ በመስጠት ከሀገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ፋብሪካው በመልካም የአመራረት ትግበራ ሂደት ላይ ያለ መሆኑን ጠቅሰው የመድሀኒት ጥራትን በማስጠበቅ የሰው ሀይልን ከቴክናሎጂ ጋር አቀናጅቶ ለጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠት ጥራትን የሚያስጠብቅ እና የሚያረጋግጥ የማምረትን ስልትን መከተል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕ/ር አፈወርቅ ካሱም ከ7 ዓመት በፊት ሂውማንዌል ስራዎች ሲጀምር የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ በአሁን ወቅት ፋብሪካው የማምረት አቅሙን በማሳደግ በሀገር ውስጥ የመድሃኒት አቅርቦት ከፍተኛ ድርሻ መውሰዱን እና ኤክስፖርት ማድረግ መጀመሩን አመስግነው፤ የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በተሰጠው ተግባር እና ኃላፊነት መሠረት በተለይም ለሀገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሰጠውን ሁለገብ ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀው ኢንስቲትዩቱ በሕክምና ሙከራ፣ በባዮኢኩቫለንስ እና በባዮአናሊቲካል አገልግሎት በሀገርም እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ የላቀ ማዕከል እንዲሆን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ ከፋብሪካው ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልፀዋል።
ሂውማንዌል ፋርማሲዩቲካል ኢትዮጵያ በመድሃኒት አቅርቦት ያለው ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑን እና በተሰጣቸው ጊዜ የሚያቀርቡ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ ናቸው።
በጉብኝቱ መደሰታቸውን የጠቀሱት የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሚስተር ሊንግ ዜንዮንግ የተሰጧቸውን አስተያየቶች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን እንደሚጠቀሙበት የገለፁ ሲሆን የሀገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካል ምርታማነትን ለማሳደግ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተቀናጅተው ወደ ፋብሪካው በመምጣታቸ የተደሰቱ መሆናቸውን ገልፀው የሚመለከታቸው የዘርፋ የመንግስት አካላት የተቀናጀ ድጋፋዊ አሰራር እንዲቀጥል ሲሉ ጠይቀዋል።



