
ፌስቲቫሉ “ውጤታማ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ትግበራ ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ቃል በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ተካሂዷል።
የበለፀገ ሃገር ለመገንባት የዜጎችን ጤንነት የማረጋገጥ አስፈላጊነት አጽንኦት በመስጠት የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንደሻው ጣሰው የተናገሩ ሲሆን፤ ምርታማነትን ለመጨመር የህብረተሰብ ጤናን ማስጠበቅ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል የማህበረሰቡን የአገልግሎት እርካታ ለማሳደግ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መትጋት አለባቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለክልሉ ህዝብ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን አመስግነዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት የጤና ፖሊሲያችን መሰረት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ናቸው። መንግስት ጤንነቱ የተጠበቀ ዜጋ ለመፍጠር የጤና አገልግሎት ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።
ይህንንም ለማሳካት የጤና ተቋማትን ማስፋፋት እና የጤና ባለሙያዎችን የማፍራት ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳት ዶ/ር መቅደስ፤ እንደ ወባ ያሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል ግንባር ቀደም በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን አመስግነዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ትግበራ ለማሻሻል ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስነድ በክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ቀርቦ በመድረኩ ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።
በክልሉ በጤናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን የሚያሳይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን የቀረበ ሲሆን፤ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እውቅና ተሰጥቷል።
የመድኃኒት እና የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ለክልሉ የተደረገ ሲሆን፤ የጤና ተቋማትን የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የኮሙኒኬሽን መሣሪያዎች ድጋፍም ተደርጓል።


