
ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው
የጤና አገልግሎት ስርዓትን ለማዘመን የበለጸጉ ሶፍትዌሮች እና በተገነቡ ጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁስ ለማሟላት ድጋፍ ያስፈልጋል ፦
ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው
ሆሳዕና፣የካቲት 23/2017ዓ.ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ለኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና ለስራ ባልደረቦቻቸው በጽ/ቤታቸው አቀባበል አድርገዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ከልኡካን ቡድኑ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ተመስርቶ ወደ ተግባር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የጤና ሚኒስቴር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ክልሉ ሲመሰረት ከነባሩ ክልል የተላለፈ ከፍተኛ የእዳ ጫና እንደነበር የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ከ4 ነጥብ 8 እስከ 5 ቢሊየን ብር እዳ ስለመከፈሉ አብራርተዋል።
ምንም እንኳን ክልሉ በበርካታ የበጀት ጫናዎች ውስጥ ቢያልፍም በተለያዩ ከተሞች 7 የቢሮ ግንባታ ስራ መጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ርዕሰ መስተዳድሩ ለልኡካን ቡድኑ አብራርተዋል።
መንግስታዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ህንጻዎች በሁለት አመት ከስድስት ወራት ማጠናቀቅ የሚያስችል ግብ ተቀምጧል ብለዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው የተጓተተውን የወልቂጤ ሆስፒታል ለውጤት ማብቃት እንዲቻል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ርዕሰ መስተዳድሩ ትብብር ጠይቀዋል።
የጤና ስርዓትን ከማዘመን አንጻር የበለጸጉ ሶፍት ዌሮች እንደሚያስፈልጉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በክልሉ በርካታ ጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች መገንባታቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ የህክምና ቁሳቁስ በማሟላት ረገድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር )በአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት እንዲገነባ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በክልሉ 90 ፕሮጀክቶችን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
ፕሮጀክቶቹ 1ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የሚጠይቁ ሲሆን ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው በክልሉ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል።
ክልሉ በአጭር ጊዜ ተመስርቶ በፍጥነት ወደ ልማት መግባቱን ሚኒስትሯ አድንቀዋል።
የክልለን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የክልሉ መንግስት የወሰደው ቁርጠኛ አቋም የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በጤና ተቋማት ግንባታ፣በማህበረሰብ ጤና መድህን እና በሌሎችም የጤና ልማት ስራ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን በአብነት ጠቅሰዋል።
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ በየደረጃው ያለው መላው አመራር ለጤና ልማት ስራ በሰጠው ልዩ ትኩረት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በወልቂጤ ሆስፒታል ግንባታ ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ተጨማሪ ውይይት እና ጥናት እንደሚካሔድ አብራርተዋል።
በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚሰራም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።



