
(ሆሳዕና፣የካቲት 23/2017 )በጤና ሚኒስተሯ የተመራ ልዑክ በጉራጌና ሀድያ ዞኖች በጤናዉ ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ጎብኝቷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንዳሉት በክልሉ በጤና ተቋማት ላይ እየተካሔደ ያለው ምልከታ መልካም ልምዶችን ማስቀጠል እና በአፈጻጸም ረገድ የተስተዋሉ ውስንነቶችን ማረም የሚያስችል ነው ብለዋል።
በዚህም በጉራጌና በሀድያ ዞኖች በጤናዉ ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በወልቂልጤ ከተማ በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የሚሰጥባቸውን የጤና አጠባበቅ ተቋማት በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
በከተማው ግንባታዉ ተጀመሮ ያልተጠናቀዉን ሆስፒታልን ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይሰራል ሲሉም አመላክተዋል።
በሀድያ ዞን የሚገኘውን የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይድ ሆስፒታል ለበርካታ ዜጎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በወሊድ አገልግሎት ፡ በእናቶችና ህፃናት ፡ የህክምና አገልግሎትን በመስጠት ለረዥም ዘመን ያገለገለ ሆስፒታል ቢሆንም የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ በርካታ ጥያቄ ሲነሳበት የነበረ ሆስፒታል ስለመሆኑም አስታዉሰዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተቋሙ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን ከተቋሙ አመራሮች ጋር ለመፍታት በሰራዉ ስራ ተጨባጭ ዉጤት ማምጣት መቻሉን በምልከታዉ ማረጋገጥ የተቻለበት ስለመሆኑም ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ የፅኑ ህሙማን የህክምና አገልግሎት መስጫ ፅዱ ከማድረግ ጀምሮ በሆስፒታሉ በርካታ መሻሻሎች የታየበት ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከህክምና አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከማህበረሰቡና ከጤና ባለሙያዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብ ያጠናክራልም ነዉ ያሉት፡፡
ሚኒስቴሩ የተሟላ የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሚደረግበትን ስርዓት ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በክልሉ በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል የሆኑ ሆስፒታሎችን መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
በጤና ተቋማት ግንባታ ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ስለመሆኑም ኃላፊው በአብነት ጠቅሰዋል።
በክልሉ የአጠቃላይ ጤና ኬላ ግንባታ በስፋት መካሔዱን የገለጹት አቶ ሳሙኤል ይህም የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ከመከላከል ስራ እስከ ህክምና ባለው ሂደት የህብረተሰቡ፣የአመራሩ እና የባለሙያው የተቀናጀ ትብብር እና ጥረት ውጤታማ ስለመሆኑም ኃላፊው አመላክተዋል።
የህክምና ቁሳቁስ ግብአት አቅርቦት ለዘርፉ ስራ በተግዳሮትነት የሚጠቀስ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል በተለይ የመድሀኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ በአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት አማካኝነት በህብረተሰብ ተሳትፎ የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶች መገንባት የሚያስችል ስርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።
ይህም በመድሀኒት አቅርቦት ላይ የሚያጋጥመውን ችግር ለመቅረፍ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም ኃላፊው አመላክተዋል።
የጤናውን ዘርፍ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ የህዝቡን የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅም ኃላፊው አስረድተዋል።
በመስክ ምልከታው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፣የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ሌሎች የክልል እና የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በተስፋዬ መኮንን




