Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የሕብረተሰብ የጤና አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱና ፈተና እየሆኑ ስለመጡ የጤና ስርዓቱ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ሊኖረው ይገባል፡- የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ::

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት10ኛውን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ፎረም ”የማይበገር የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስርዓት ለብሄራዊ ጤና ደህንነት” በሚል መሪ ቃል በሃዋሳ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ ዛሬ እዚህ የደረስነው እንደሃገር በተለያዩ ጊዜያት ሲፈትኑን የነበሩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በጋራ ምላሽ በመስጠት ነው፤ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የጤናው ዘርፍ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዓለምን እየፈተኑ ያሉ የህብረተሰብ የጤና አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱና እንደ ሃገርም ፈተና እየሆኑ ስለመጡ የጤና ስርዓታችን ይህንን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ሊኖረው እንደሚገባ ዶ/ር አየለ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ይህ ፎረም ዘርፈ ብዙ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ተግባራትን በሁሉም መዋቅሮች ውጤታማ እዲሆኑ ለማስረጽ ትልቅ ዕድል የሚፈጠር መድረክ ነው ብለዋል፡፡

መድረኩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስራዎችን የምንገመግምበት፣ የገጠሙንን ችግሮች መንስኤዎች የምንፈትሽበት፣ ቀጣይ አቅጣጫዎች የምናስቀምጥት እንዲሁም አዲስ የተከሰቱና በድጋሜ የሚከሰቱ የሕብረተሰብ የጤና አደጋዎችን ለመከላከል መፍትሄ የምናፈላልግበት መድረክ እንደሆነ ዶ/ር መሳይ ገልጸዋል፡፡

የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስራን ውጤታማ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ በሽታዎች ሳይከሰቱ በፊት የሚከናወኑት የዝግጁነት ተግባራት ናቸው ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ ናቸው፡፡

የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በዚህ መድረክ የሕብረተሰባችንን የጤና አደጋ ለመከላከል የሁላችንም ቁርጠኝነት የምናሳይበት መሆኑን ገልጸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የጤና አደጋዎች በአይነትና በቁጥር እየተስፋፉ ስለመጡ ፈጣን ምላሽ መስጠት በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ኮሚሽነር ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ”የቤተሰብ ኃላፊነትና የማህበረሰብ አጋርነት ለሁሉም አይነት አደጋዎች አይበገሬነት!” የሚል ጽሁፍ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ፎረም ላይ የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የክልል የጤናው ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ኮሚሽንና የፌዴራል ፖሊስ ጤና ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *