
ጥር 20/2017 ዓ/ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሳምንታዊ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል EOC ሳምንታዊ ግምገማ አካሂዷል።
የቢሮው ጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ከለላው አቻምየለህ የሳምንቱን ሪፖርት ሲያቀርቡ ባለፈው ሳምንት የነበረው የወባ ጫና በዚህ ሳምንት 2.1% ጭማሪ አሳይተዋል ብሏል። ባለፈው ሳምንት 6685 የነበረው በዚህ ሳምንት 6828 መሆኑን ገልጿል ከነዚህም ሀድያ ፣ ስልጤ ፣ ጉራጌና ከምባታ የክልሉን 75.2% እንደሚሸፍኑ ገልፀዋል ። በሪፖርቱ የእናቶች እና ህፃናት የምግብ እጥረት ሁኔታ : በአንዳንድ አከባቢዎች የኩፍኝ ወረርሽኝ ሁኔታ በሪፖርቱ ተነስቷል ።
ውይይቱን የመሩት የክልሉ ጤና ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በክልል ደረጃ የወባ በሽታ ለመግታት እና ዜጎች እንዳይሞቱ ለማድረግ በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ስርጭቱ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰዉ የወባ ጫና በሚፈለገዉ ልክ እንዲቀንስ እና በቀጣይ ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል የንቅናቄው ስራ እና ግንዛቤ የመፍጠር ተግባርና የላቦራቶሪ የወባ ምርመራ ቁጥር መጨመር ይገባል ብለዋል።
ከወባ በሽታ እና ከሌሎች ከተለያዩ ድንገተኛ በሽታዎች ነፃ የሆኑ አካባቢዎችን ለመፍጠር የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እና የየግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በማጠናከር ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ማሙሽ የባለፈዉን ተሞክሮ በቀጣይ በማጠናከር ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ቀድመን በመተንበይ መዘጋጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አቶ ማሙሽ አክለውም የከፍተኛ የምግብ እጥረትና የኩፍኝ በሽታና የልጅነት ልምሻ በሽታዎች ላይ ሁሉም መዋቅሮች ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በመድረኩም አቶ ማሙሽ በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች በቀጣይ ቀናቶች ለሚደረገው የልጅነት ልምሻ ክትባት ዙሪያ ሁሉም መዋቅሮች ቅድመ ዝግጅት አድርገው ዝግጁ መሆናቸውን ለክልሉ ማሳወቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል። በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በሳምንቱ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። በውይይቱ የክልል ጤና ቢሮ እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሞያዎች እና የሁሉም ዞን እና ልዩ ወረዳዎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል ።
የማ/ኢት/ክ/ጤና ቢሮ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

