
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በመድረኩ እንደተናገሩት ስብሰባው የወባ መድሃኒቶችን ወጪ ለመቀነስ እና ወባን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማጎልበት የሚስችሉ ስልቶች ላይ ለመወያየት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
የወባ በሽታን ለመከላከል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊነት እና ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ዶ/ር መቅደስ የተናገሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አጠባበቅ ተቋሞችን ማጠናከር እና የመከላከል ስራዎችን ማጎልበት ከጥረታቸው ግንባር ቀደም መሆን እንዳለበት ለአጋር ድርጅቶች አስረድተዋል።
የወባ ስርጭትን ከመቀነስ ረገድ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ያስረዱ ሲሆን፤ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭት ያሉ ምክንያቶች የበሽታውን ስርጭት እንዳባባሱት ጠቁመዋል። ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰብ፣ በተለይም ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ፣ እንዲሁም ከጎረቤት ሃገር የሚገቡ ስደተኞች፣ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በልማት ኮሪደሮች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ መለየቱን ተናግረዋል።
ዶ/ር ደረጄ አያይዘውም ጤና ሚኒስቴር በየሳምንቱ የወባ ስርጭት የሚመለከት ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ሲያደርስ መቆየቱን አስታውሰው፤ በተሰራዉ የተቀናጀ ስራ ዝቅተኛ ከወባ ጋር ተያይዞ የሚደርስ ሞት መመዝገቡን ጠቁመዋል።
የጌትስ ፋውንዴሽን የስትራቴጂ ኤንድ ካንትሪ ፓርትነርሺፕ ዳይሬክተር የሆኑት ብሩኖ ሙኔን እንዳሉት የጌትስ ፋውንዴሽን ዋና አላማ የወባ በሽታን ማጥፋት ነው። የፋውንዴሽኑ ስትራቴጂካዊ ግቦች ደግሞ ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት ያለባቸውን ሃገራት ሸክም መቀነስ፣ የበሽታውን ማጥፋት ዘመቻ ማፋጠን እና በሽታው መድሃኒት ከመቋቋሙ በፊት አስቀድሞ ዝግጅቶችን ማድረግ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
በመድረኩ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከጌትስ ፋውንዴሽን እና በተለያዩ አጋሮች የተገኙ ሲሆን በቀጣይ የወባ ስርጭትን ለመግታት የአጋር ድርጅቶች ሚና ምን መሆን እንዳለበት በመድረኩ መግባባት ላይ ተደርሷል፡

