Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የጤናማ እናትነት ወርን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

የጤናማ እናትነት ወርን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክ/መ/ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ጋዜጣዊ የሰጡ ሲሆን በሀገራችንና በክልላችን ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የጤናማ እናትነት ወር “ጥራቱን የጠበቀ የምጥና የወሊድ እንክብካቤ ለሁሉም እናት፣ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልጸዋል።

የጤናማ እናትነት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ያለዉ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሳሙኤል በአገራችን ብሎም በክልላችን ባለፉት አመታት በተሰሩ ስራዎች አበረታች ለውጦች መምጣታቸውን አመላክተዋል።

ባለፉት ጊዜያት በተደረገው ርብርብ የእናቶችን የሞት ምጣኔ 72.8% በመቶ መቀነስ እንደተቻለ የገለጹት ኃላፊው በዚህም ረገድ በክልላችን የጤና አገልግሎት ተደረሽነት እና ፍትሃዊነት ላይ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማ ከማድረጉም ባሻገር አበረታች ለውጦች እንዲመጡ ጉልህ አስተዋጽኦ ማርከቱን አስረድተዋል፡፡

የጤናማ እናትነት ተግባር በ2030 ለማሳካት በዕቅድ ከተያዙት የልማት ግቦች አንዱ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሳሙኤል በክልላችንም የእናቶችን ጤና ለማሻሸልና ሞት ለመቀነስ የየተለያዩ ተግባራትን በማከናወን የሚከበር ይሆናልም ብለዋል፡፡

የጤናማ እናትነት ወር ጥር ብቻ ተከብሮ የሚያበቃ ተግባር አለመሆኑን በማስገንዘብ አመቱን ሙሉ በክልሉ ያሉ ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች በትኩረት ሊሰሩበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በጥር ወር በሚከበረዉ የጤናማ እናትነት ወር ከእርግዝናና ወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ህመምና ሞትን ለማስቀረት ከባለድረሻ አካላት ጋር በቅንጅት የቅድመ እርግዝና ጤና አገልግሎት፣ የተቀናጀ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን፣ የቅድመ ወሊድ ክትትል ተደራሽነትን በሁሉም ጤና ተቋማት የማረጋገጥ፣ በጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች በሰለጠና ባለሙያ የወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከጤና ጣቢያዎች ርቀት ላይ ለሚገኙ እናቶች ደግሞ በጤና ተቋማት የእናቶች ማቆያ ቤቶችን መገንባት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሳሙኤል አክለው ገልጸዋል።

አምቡላንስ ተገቢው አገልግሎት እንዲሰጥ ድጋፍና ክትትል የማድረግ፣ የደም አቅርቦትን ማሳደግ፣ የነፍሰጡር እናቶች ለይቶ መመዝገብና ኮንፍረንስ በማድረግ በአቅራብያ ያሉ ጤና ተቋማት ላይ አገልግሎት እንዲያገኙ መላው ህብረተሰብ በንቃት በማሳተፍና ሀብት በማሰባሰብ የእናቶችን ጤና ለማሻሸል ሰፊ ሥራ በንቅናቄ መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ39ኛ ጊዜ እንዲሁም በአገራችንና በክልላችን በ2017 ዓ.ም ለ19ኛ ጊዜ “ጥራቱን የጠበቀ የምጥና የወሊድ እንክብካቤ ለሁሉም እናት፣ ለጤናማ እናትነት”! በሚል መሪ ቃል የጤናማ እናትነት ወርን ስናከብር፤ ስለ እናቶች እና ህጻናት ጤና ትክክለኛ መረጃ በማድረስ የሚዲያ ባለሙያዎችም የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የጤናማ እናትነትን ጉዳይ ሁል ጊዜ ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ መስራት እንደሚገባ በማሳሰብ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስለ ማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎችን እንዲሰሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የማ/ኢት/ክ/ጤና ቢሮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *