
ጥር 13/2017 ዓ/ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሳምንታዊ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል EOC ሳምንታዊ ግምገማ አካሂዷል።
የቢሮው ጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሐመድ ያሲን የሳምንቱን ሪፖርት ሲያቀርቡ ባለፈው ሳምንት የነበረው የወባ ጫና በዚህ ሳምንት 13% ቅናሽ አሳይተዋል ብሏል። ባለፈው ሳምንት 7675 የነበረው በዚህ ሳምንት 6685 መሆኑን ገልጿል ከነዚህም ሀድያና ስልጤ፣ ጉራጌ ፡ ከምባታ የክልሉን 74.9% እንደሚሸፍኑ የገለጹ ሲሆን ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር 13% በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል ።
በዚህ ሳምንት በወባ በሽታ ምክንያት የአንድ ሰው ሞት የተከሰተ ሲሆን ይህም ከሀዲያ ዞን ሪፖርት መደረጉን ገልጾ በአጠቃላይ የተኝቶ ታካሚዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ከቀረበው ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የክልሉ ጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክተሬት ዳይሬክተር አቶ ወልደሰንበት ሸዋዓለም እንደገለጹት በክልል ደረጃ የወባ በሽታን ለመግታት እና ዜጎች እንዳይሞቱ ለማድረግ በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት መቀነስ መቻሉን ጠቅሰው አሁንም የወባ ጫና በሚፈለገው ልክ እንዲቀንስ እና በቀጣይ ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል የንቅናቄው ስራ እና ግንዛቤ የመፍጠር ተግባሩ በየመዋቅሮች ተጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በነበረዉ በአጠቃላይ በህብረተሰብ ተሳትፎ ትምህርት ቤቶች ላይ፣ከሀይማኖት ተቋማት ጋር፣ ቤት ለቤት ጉብኝት በማድረግ ፣ የአጎበር አጠቃቀም መጠናከር እና መሠል ተግባራት ዙሪያ በተደረገው ከፍተኛ የንቅናቄ ስራ የወባ በሽታ መቀነሱን ጠቁመዋል።
ሌሎች ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በማጠናከር ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ወ/ሰንበት አሁንም የአየር ንብረት ሁኔታን በተላይም የዝናብ ድንገት ቢከሰት የወባ ደጋሚ የማገርሸት ዕድል ልኖር ስለሚችል የባለፈዉን ተሞክሮ በማጠናከር ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታን ቀድመን በመተንበይ መዘጋጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አቶ ወልደሰንበት አክለውም ከየመዋቅሩ የሚላኩ ሪፖርት እና መሬት ያለው አፈፃፀም የማይመጣጠን ስለሆነ የተደራጀ እና ተአማኒነት ያለዉን መረጃ ማደራጀት እንደሚገባ ገልፀው በቀጣይ ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለዉን የዉሃ እጥረት ተሳቢ በማድረግ ህብረተሰቡን ከጤና ስጋት ለመታደግ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩም በክልሉ የወባ ወረርሽኝ እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በሳምንቱ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የማ/ኢት/ክ/ጤና ቢሮ

