የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ እያደራጀ ላለው የሪፈረንስ ላብራቶሪ የሚያግዝ ፣ ለኤች አይ ቪ/ኤድስ እና ሌሎች ተህዋስያንን መጠን (Viral Load) መመርመርያ ማሽን ተረከበ።
ቀን: 29/02/2017 ዓ.ም. ፤ ወራቤ
የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ፣ በክልሉ የመጀመርያ የሆነውን እና ለኤች አይ ቪ/ኤድስ እና ሌሎች ተህዋስያንን መጠን (Viral Load) መመርመርያ ማሽን፣ ዛሬ በወራቤ ከተማ መረከቡ ተገለፀ።
ክልሉ ይህን የMolecular Testing ማሽን የተረከበው፣ በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) አማካኝነት ከጀርመኑ ኩባንያ Abbott GMBH፣ የኢትዮጵያ ወኪል ከሆነው ሳብ-ሳሕራን ባዮሜዲካል ሲሆን፤ መመርመርያ ማሽኑ በተለይም ለኤች አይ ቪ/ኤድስ ህሙማን፣ የሚወስዱት የፀረ-ኤች አይ ቪ ተህዋስ መድሃኒት በደማቸው ውስጥ የሚገኘውን ተህዋስ በመቀነስ እንዲሁም የማይለካ እና የማይተላለፍበት ደረጃ እንዲደርስ ከማድረግ አንፃር፣ የመድሃኒቱን ፍቱንነት ለማረጋገጥ ይረዳል።
የክልሉ ሕ/ጤ/ኢ ዳይሬክተር ጀነራል፣ አቶ ማሙሽ ሁሴን፤ የክልሉ ሕ/ጤ/ኢ ላቦራቶሪ ይህን ማሽን በመረከቡ ደስታቸውን ገልፀው፣ ለዚህ ስኬት ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) ከአንድ አመት በላይ ሲወያይ መቆየቱንና፤ በቀጣይም የማሽኑን ተከላ በማድረግና የሚያሰፈልጉ ሁኔታዎችን በመሟላት፣ የክልሉ ላቦራቶሪ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለማድረግ፣ ኢንስቲትዩቱ ቁርጠኛ መሆኑን እና ጠንክሮ እንክሮ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የMolecular Testing ማሽኑን የተረከቡት የክልሉ ሕ/ጤ/ኢ ላቦራቶሪ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አተ ክብረአብ ገብረህይወት በበኩላቸው፣ በክልሉ ይህ ማሽን ባለመኖሩ ምክንያት፣ በክልሉ የሚገኙ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ህሙማን፣ በደማቸው ውስጥ የሚገኘውን የHIV ተህዋስ መጠን ለማስመርመር፣ የደም ናሙናዎችን ወደ ሃዋሳ እና አዲስ አበባ እየተላከ የቆየ ሲሆን፣ የምርመራ ውጤት ለማግኘት ህሙማን እስከ ሁለት ወራት ለመጠበቅ ተገደው መቆየታቸውና፣ ይህን ማሽን የክልሉ ላቦራቶሪ መረከቡ፣ በተለይም ለHIV/AIDS ህሙማን ትልቅ እፎይታ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ M-2000 የተሰኘው የጀርመኑ Abbott GmBH ምርት የሆነው የMolecular Testing ማሽን፣ የደም ናሙናን በመጠቀም የHIV/AIDS ተህዋስ መጠንን (HIV Viral Load) ከመለካት ባለፈ፣ የHepatitis B እና C ተህዋስ መጠንን፣ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍ የጨቅላ ህፃናት HIV/AIDS ምርመራ፣ ለማህፀን በር ካንሰር (Human Papilloma Virus) እና ሌሎችም ምርመራ በስፋት እያገለገለ ሲሆን፣ በግማሽ ቀን ውስጥ ከ180 በላይ ናሙናዎችን መመርመር እንደሚቻል ተገልጿል።
በመጨረሻም የክልሉ ሕ/ጤ/ኢ ዳይሬክተር ጀነራል፣ አቶ ማሙሽ ሁሴን፤ ለተደረገው ድጋፍ እና አስተዋፅኦ፤ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI)፣ የAbbott GMBH ኩባንያ የኢትዮጵያ ወኪል ለሆነው ሳብ-ሳሕራን ባዮሜዲካል እና ምስጋናቸውን ገልፀዋል።
መረጃው- የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው።