በክልሉ እየታየ ያለውን የወባ በሽታ መስፋፋትና ጉዳት እየቀነሰ ያለ ሲሆን ለመከላከል ሥራ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ነው፦የክልሉ ጤና ቢሮ
ሆሳዕና፦ህዳር 4/2017ዓ.ም
በክልሉ እየተስፋፋ የመጣውን የወባ በሽታ በተቀናጀ መንገድ በመከላከል ላይ እየተሰራ ባለው ሥራ ከፍተኛ መሻሻል ያለ ሲሆን ከሁሉም የወጣት አደረጃጀቶች በንቃት እንዲሳተፉና ሚናቸው የላቄ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገልፀዋል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በክልሉ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ የነበረውን የወባ በሽታ በጋራ እንዴት መመከት እንደሚቻል ከክልሉ ወጣቶች ሊግ አመራር ጋር መክረዋል።
የወጣት ሊጉ አመራሮችና አባላት በየአካባቢው በንቅናቄ በመንቀሳቀስ ህብረተሰቡ ስለበሽታው የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኝና የተቀናጁ የመከላከል ስራዎች እንዲጠናከሩ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ በርካታ ህዝብ በወባ በሽታ እየተጎዳ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ማሙሽ በሽታው የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት በጋራ መከላከል እንደሚገባም አስታውቀዋል።
በክልሉ እስከ 85 ከመቶ የሚሆነው አካባቢ ለወባ በሽታ ተጋላጭ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ሃላፊው ጠቁመው ለዚህም የአየር ንብረት ለውጥና የወባ ትንኝ ቁጥር መጨመር መንስኤ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
በሽታው ቀድሞ በቆላማ አካባቢዎች ተወስኖ የቆየ ቢሆንም አሁን በአንዳንድ ደጋማ አካባቢዎችም ጭምር እየተከሰተ በመምጣቱ ህብረተሰቡ በሁሉም አካባቢ ቀድሞ የመከላከል ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ማሙሽ ሁሴን ጥሪ አቅርበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወጣት አብዱ ድንቁ በክልሉ የተከሰተውን የወባ በሽታ ለመቀልበስ የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤቱ የተለያዩ የንቅናቄ ስራዎችን እንደሚያካሂድ አመልክተዋል።
“እኔ እያለሁ አንድም ህጻን/አንድም ነፍሰ ጡር እናት በወባ አትሞትም”በሚል መሪ ቃል የንቅናቄ ስራዎችን በማካሄድ በሽታውን ለመግታት እንደሚሰራ ወጣት አብዱ አስታውቋል።
ወቅቱ ተማሪዎች ትምህርት የጀመሩበትና ምርት እየተሰበሰበ ያለበት በመሆኑ የሊጉ አደረጃጀቶች መላውን ህዝብ በማንቀሳቀስ የከፋ የወባ ጉዳት ከመከሰቱ በፊት መከላከል እንዲችሉም ጥሪ አቅርቧል።
ወጣት አብዱ አክሎም ሁሉም የሊጉ አመራሮችና አባላት የቤት ለቤት አሰሳ ስራዎችን በማጠናከር ህመምተኞችን ወደ ጤና ተቋም እንዲወስዱ ፣”በጎነት በሆስፒታል”በሚል መሪ ቃልም ታማሚዎችን ጤና ተቋም ሄዶ መጠየቅና የድጋፍና ክትትል ስራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
ሊግ ጽህፈት ቤቱ እያደረገ በሚገኘው የሩብ ዓመት ዕቅድ ግምገማ መድረክ የተገኙት አቶ ማሙሽ ሁሴን በክልሉ የተከሰተውን የወባ በሽታ ከወጣት አደረጃጀቶችና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በጋራ ለመከላከል ቢሮው አቅዶ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።