በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት አለም አቀፍ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሲሙሌሽን ልምምድ ከ73 በላይ የሆኑ ሃገሮች የሚሳተፉበት ተግባራዊ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሲሙሌሽን ልምምድ ሲሆን፤ ለቀጣይ ሶስት ቀናት በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚካሄድ ይሆናል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት ኢትዮጵያ መድረኩን ማዘጋጀቷ መንግስት ሁሉንም ዜጎች የሚያገለግል እና የሚጠብቅ የጤና ስርዓት ለመገንባት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል። የጤና አጠባበቅ ተደራሽነትን በማስፋት፣ የጤና አገልግሎትን ጥራት በማሻሻል እና የጤና ውጤቶችን በመላ አገሪቱ በማሳደግ ረገድ የተገኙ እመርታዊ ዉጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
የጤና አገልግሎትን ለማጠናከር ያለን ቁርጠኝነት የበሽታ ክትትልን ዲጂታላይዝ እስከ ማድረግ ድረስ ይዘልቃል ያሉት ዶ/ር መቅደስ፣ ይህም የህዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን በበለጠ ፍጥነት እና ትክክለኛ ምላሽ እንድንሰጥ ያስችለናል ብለዋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ ደረጃዎች የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ ምላሽ መስጫ ማዕከላት መቋቋማቸውን እና ይህም ሀገራዊ የጤና ደህንነታችንን ለማጠናከር ማስቻሉን አብራርተዋል። እ.ኤ.አ. በ2023 የጋራ የውጭ ግምገማ ላይ እንደተገለፀው ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ የጤና ደንቦችን መስፈርቶች በማሟላት በተለይም በድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ አቅም ላይ ትልቅ እድገት ማሳየቷን በማስታወስም፤ ሀገራዊ የህብረተሰብ ጤና ጂኖሚክ ላብራቶሪ እና በመላ ሀገሪቱ የተሟላ ላብራቶሪዎችን በመገንባት ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚያስችል እቅም መገንባት መቻሉን አክለዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤናን፣ የድንገተኛ አደጋ አስተዳደርን፣ የህብረተሰብ ጤና ጥናትና ምርምርን፣ ማስረጃ የማመንጨት፣ እና የላብራቶሪ አቅምን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ የህዝብ ጤና ስርአቶችን በማጠናከር እና ለህዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ዝግጁነት እና ምላሽን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ለመከላከል እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችላትን አቅም መገንባቷን የአለም ጤና ድርጅት እንደሚረዳ የተናገሩት የድርጅቱ የጤና ድንገተኛ አደጋ ምላሽ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚሼል፤ የሲሙሌሽን ልምምዱ በሃገራት መሃል ትስስርን በመፍጠር የተሻለ አለም አቀፍ የበሽታ መከላከል አቅምን ለመፈጠር ያስችላል ብለዋል።
ሲሙሌሽኑ የሚካሄደው በአለም አቀፍ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች እና ድንበር ተሸጋሪ ቀውሶች የሚሰጠውን ዓለም አቀፍ ምላሽ በማጠናከር፣ በሕዝብ ጤና ላይ በየቀኑ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች በሲሙሌሽን በመለማመድ ልምድ ለመጋራት ነው ያሉት በአለም የጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ካንትሪ ምክትል ተወካይ ዶ/ር ዲላሚኒ ሲሆኑ፤ የአለም ጤና ድርጅት ተልእኮዎች ጤናን ማስተዋወቅ፣ የአለምን ደህንነት መጠበቅ እና አቅመ ደካሞችን ማገልገል መሆኑን ገልጸዋል።
የአለም ጤና ጥበቃ ጥረቶችን በመምራት እና በማስተባበር፣ ደረጃዎችን በማውጣት፣ ለአገሮች የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት እና አጋርነትን በማጎልበት ይህን ተልዕኮ ለማሳካት እንደሚሰራም አክለዋል።
ህዳር 13 እና 14 ቀን 2024 በአለም ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት እና በአለም ጤና ድርጅት በጋራ አስተናጋጅነት በተዘጋጀው የአለም የጤና ድንገተኛ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሲሙሌሽን ልምምድ የአሰራር ዝግጁነት፣አቅም እና ቅልጥፍና በመሞከር ረገድ ባለድርሻ አካላትን ለማስተባበር ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ እንደሚያገለግል የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብጤ የገለጹ ሲሆን፤ በጤና ድንገተኛ አደጋዎች በአገር አቀፍ፣ በክልላዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ምላሽ ለመስጠት ችሎታዎችን ለማዳበር መታቀዱን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ግቢ ውስጥ መካሄድ የጀመረው አለም አቀፍ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሲሙሌሽን ልምምድ በጉብኝት ምልከታ ተደርጓል፡፡