Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የወባ በሽታ ወረርሽኝ አሁን ካለበት ስርጭት ደረጃ ከፍ እንዳይል የሁሉም አመራር እና የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።

ጥቅምት 5/2017

የሀላባ ዞን ጤና መምሪያ ሳምንታዊ የ (EOC)የድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምለሽ አሰጣጥ ሳምንታዊ አፈፃፀምና ወቅታዊ የወባ በሽታ ስርጭትን አስመልክቶ ውይይት በዛሬው እለት ተካሂዷል።

የድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምለሽ አሰጣጥ እና የማህበረሰብ ጤና አደጋዎችና የወባ ወረርሽኝ ምላሽ መስጠት ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩም በዞናችን ስር በሚገኙ በሁሉም መዋቅሮች የወባ ወረርሽኝ በተከሰተባቸዉ ቀበሌያት የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት በሳምንቱ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት በድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምለሽ አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ በሆኑት በአቶ ዬጎሬ ዳቆሮ የቀረበ ሲሆን በወባ በሽታ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስወገድ ዙሪያ በየደረጃዉ የተሰሩ ስራዎችን መገምገም ተችሏል፡፡

በዞናችን ወባ በሚበዛባቸው አከባቢዎች ህብረተሰቡ አጎበር አዘውትሮ ከመጠበም እና ግንዛቤ ከማስጨበጥ አኳያ እንዲሁም ያቆሩ ውሃማ አከባቢዎችን ከማዳፈን እና ወባን ከማከም አንፃር በሰፊው የተነሳ ሲሆን አሁንም የወባ ጫና ባለባቸው ቀበሌያት ከአመራር እስከ ታችኛው መዋቅር በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የመምሪያው ኃላፊ ዶ/ር ሸምሱ ረሺድ ገልፀዋል።

የወባ ማጥፋቱ ስራ ላይ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው እና ራሱን ከበሽታው መከላከል እንዲችል በየወረዳ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባም በውይይት መድረኩ በሰፊው ተነስቷል።

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እንደ ዞን የተጀመሩ የማህበረሰብ ንቅናቄ መድረኮችን ማጠናከር እና የግንዛቤ ስራው ቀጣይነት ባለው መልኩ በየመዋቅሩ ሊመራ እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።

በተለይ የወባ በሽታ ስርጭት ጫና በበዛባቸው ቀበሌያት የዞን ፎካሎችም ከወረዳዎች ጋር በመናበብ እና በመቀናጀት በተመደቡበት ቦታዎች በትኩረት መስራት ይገባልም ተብሏል።

በቀጣይም በወባ መከላል እና መቆጣጠር ስራዎች እና መደበኛ የህክምና ተግባራት ላይ ጤና ተቋማት በልዩ ትኩረት ሊተገብሩ የሚገባ እና ጤና ተቋማት አስፈላጊውን ሪፖርት በወቅቱ መላክ እንደሚገባቸው እንዲሁም በታችኛው መዋቅር የተጀመሩ የንቅናቄ ስራዎች ከወትሮ በተለየ መልኩ ማጠናከር እንደሚገባ በውይይቱ ማጠቃለያ የመምሪያው ኃላፊ ዶ/ር ሸምሱ ረሺድ አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *